ቀጥታ፡

የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና በምርጫ ሂደት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ማጠናከር አለባቸው

አዳማ፣ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ)፡- የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት የዜጎችን ንቁ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያደርጉት ጥረት ሊጠናከር እንደሚገባ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ገለጹ።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፣ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባት ምርጫን በሰላማዊና በፍትሐዊነት መንገድ ማካሄድ ወሳኝ ነው።

በዚህ ተግባር ውስጥም የሲቪል ማህበራት ሚና ከምርጫ ታዛቢነት ባሻገር፣ ህዝቡን በማስተማር ዜጎች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው በኃላፊነት እንዲቆሙ በማድረግ ረገድ አገራዊ አደራቸውን እየተወጡ መሆኑን አስረድተዋል።

ዜጎች በምርጫ ሂደት ላይ በንቃት የመሳተፍ ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ ማስተማር እንደሚገባ የጠቀሱት አቶ ፋሲካው፤ ምርጫው ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የማስገንዘብ ተግባሩ ተጠናክሮ መቀጠሉን አብራርተዋል።

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ 168 የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች የዜጎችን የምርጫ ሥርዓት ተሳትፎ ለማሳደግና 55 ማህበራት ደግሞ ምርጫውን በገለልተኝነት ለመታዘብ ፈቃድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን አባልና ቤተር ላይፍ ፎር ኦል ድርጅት ዳይሬክተር አቶ ከተማ ባህሩ በበኩላቸው፣ ፌዴሬሽኑ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ሥራ በርካታ ወጣቶችን በምርጫ ታዛቢነት አሰልጥኖ በተለያዩ አካባቢዎች ማሰማራቱን ተናግረው፤ ሁሉም አካላት የምርጫ ሕጉን በጥብቅ በመከተል በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስ ያለባቸው ሲሆን፣ ለዚህም ስኬት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

የወጣቶች አደረጃጀቶች የሚያደርጉት የግንዛቤና የክትትል ድጋፍ የምርጫውን ተአማኒነት ከማሳደጉም በላይ፣ የሀገሪቱን የዴሞክራሲ ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም