ኢትዮጵያ የወረርሽኝ በሽታዎችን በራስ አቅም መለየትና ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም እያጎለበተች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የወረርሽኝ በሽታዎችን በራስ አቅም መለየትና ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም እያጎለበተች ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ የወረርሽኝ በሽታዎችን በራስ አቅም መለየትና ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም እያጎለበተች መሆኗን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ገለጹ።
ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የጤና ተቋማትን በማዘመን በበሽታ መከላከልና አክሞ ማዳን ሥርዓት አቅምን ማጎልበት ያስቻለ ስኬታማ የፖሊሲና የሪፎርም እርምጃ ወስዳለች።
ይህም የጤና ተቋማትን የሕክምና ግብዓት በማሟላት የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ማጠናከር ያስቻለ ምኅዳር መፈጠሩን ገልጸዋል።
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የናሙና መመርመሪያ አለመኖር፣ የኦክስጅን ማከማቻ ፕላንትና የሆስፒታሎች የፅኑ ህሙማን ክፍሎች ክፍተት ወሳኝ ትምህርት መወሰዱን ተናግረዋል።
በዚህም የኢትዮጵያን የወረርሽኝ በሽታዎችን በራስ አቅም መለየትና ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም ማጎልበት ያስቻለ ሥራ መሰራቱን አንስተዋል።
ለአብነትም ኢትዮጵያ የነበራትን ሶስት የኦክስጅን ማምረቻ ፕላንት ወደ 83 በማሳደግ በየ50 ኪሎ ሜትር ርቀት ተገልጋዮች የሚጠቀሙበትን ምኅዳር መፍጠር መቻሉን አስረድተዋል።
የፅኑ ህሙማን ሕክምና ክፍል ያላቸው ሆስፒታሎች ከ70 በላይ እንዳልነበሩ በማስታወስ፤ በአሁኑ ወቅትም ወደ 198 ሆስፒታሎች ማሳድግ መቻሉን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በጤና ዘርፍ የተከናወኑ ውጤታማ የሪፎርም እርምጃዎች ኢትዮጵያ የወረርሽኝ በሽታዎችን በራስ አቅም መለየትና ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም ማጎልበት እያስቻላት ነው ብለዋል።
ለዚህም በቅርቡ ተከስቶ የነበረውን የማርበርግ ወረርሽኝ ሙሉ በሙሉ በራስ አቅም መለየትና መከላከል ያስቻለ ውጤታማ ሥራ መሰራቱን አስረድተዋል።
በወቅቶች መፈራረቅ ሳቢያ የሚከሰቱ የወባና መሰል በሽታዎችን ሥርጭት መግታት የሚያስችል የበሽታ ልየታና ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋቱንም አንሰተዋል።
በትምህርትና ስልጠናም የበሽታ ሥርጭትን ቀድሞ መከላከልና አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ብቁና ፕሮፌሽናል ሙያተኛ በማሰማራት ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ውጤታማ የቅኝት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።