የሲቪክ ማህበራት እና የሃይማኖት ተቋማት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ ይገኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
የሲቪክ ማህበራት እና የሃይማኖት ተቋማት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ ይገኛሉ
አዲስ አበባ፤ግንቦት 14/2018(ኢዜአ)፦የሲቪክ ማህበራት እና የሃይማኖት ተቋማት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአጀንዳዎች ቀረጻ ግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ከሃይማኖት ተቋማት እና ከሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ጋር እያካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ የሲቪክ ማህበራት እና የሃይማኖት ተቋማት ኮሚሽኑ እስከ ወረዳ ድረስ ወርዶ ላከናወናቸው ተግባራት ካደረጉት እገዛና ድጋፍ አንጻር የሂደቱ ባለቤት መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በተለይም ኮሚሽኑ ባለፉት ዓመታት ጉዞ ውስጥ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች እና የሲቪክ ማህበር ተወካዮች ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ መቆየታቸውን አውስተዋል።
የሃይማኖት ተቋማት እና የሲቪክ ማህበራት በአመራሮቻቸው አማካኝነት እስከ ወረዳ ድረስ በመድረስ ለተከናወኑት ስራዎች መሳካት ግንባር ቀደሞቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አህመድ ሁሴን በበኩላቸው፤ የተጀመረው የሀገራዊ ምክክር ሂደት በሀገሪቱ ያሉ ልዩነቶችን በምክክርና በመግባባት ለመፍታት የሚያስችል ጠቃሚ መድረክ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህን መልካም አጋጣሚ ሁሉም አካላት በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የሀገራዊ ምክክር አጀንዳዎችን ይበልጥ አካታች እና ታማኝ ለማድረግ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ የሲቪክ ማህበራት እና የሃይማኖት ተቋማት በባለቤትነት መንፈስ ሊሳተፉ እንደሚገባ ተናግረዋል።