ቀጥታ፡

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድበትን ዕለት በከፍተኛ ዝግጁነት እየጠበቅን ነው - የአዋሽ ሰባት ከተማ ወጣቶች 

አዋሽ ሰባት፣ ግንቦት 14/2018(ኢዜአ) ፡-ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድበትን ዕለት በከፍተኛ ዝግጁነት እየተጠባበቁ መሆናቸውን የአዋሽ ሰባት ከተማ ወጣቶች አስታወቁ።

ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ጋር ቆይታ ያደረጉት ወጣቶቹ፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን አዎንታዊ ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወጣት ራዚያ የሱፍ፤ “ይህ ጠቅላላ ምርጫ በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲጠናቀቅና የምንፈልገውን የፖለቲካ ፓርቲ በነፃነት መምረጥ የምንችልበት ምቹ አጋጣሚ ነው” ስትል ገልጻለች።

ምርጫ ወደ ሥልጣን ለመውጣት ብቸኛውና ሕጋዊው መንገድ በመሆኑ፣ እኔም ለሀገሬና ለራሴ የሚበጀውን የፖለቲካ ፓርቲ በነፃነት መርጬ ድምፄን ለመስጠት በመጠባበቅ ላይ እገኛለሁ ስትል ገልጻለች።

ወጣት ኡመር መሐመድ በበኩሉ፤ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በየሚዲያውና በመድረኮች የሚያቀርቧቸውን የምረጡኝ ቅስቀሳዎችና ክርክሮች በንቃት እየተከታተለ መሆኑን ገልጿል።

ወጣት ኡመር አክሎም፤ የፓርቲዎቹን አማራጮች በአግባቡ ከተመለከትኩ በኋላ፣ ለሀገሬና ለራሴ የሚበጀውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ፤ የምርጫዋን ዕለትም በታላቅ ዝግጁነት እየጠበቅኩ እገኛለሁ ሲል ገልጿል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን አዎንታዊ ድርሻ እየተወጣ መሆኑን የገለጸው ወጣት ኡመር፤ ይህ የሰላም ጥበቃ ተሳትፎው እስከ ምርጫው ዕለት ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጧል።

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ኡመር አቡበከር በበኩሉ፤ የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በተለያዩ የወጣት አደረጃጀቶች ውስጥ በመሳተፍ ንቁ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጿል።

በአሁኑ ወቅትም ድምጹን በነፃነት ለመስጠት የምርጫውን እለት በዝግጁነት እየተጠባበቀ መሆኑን አስታውቋል።

ወጣቶቹ አክለውም ምርጫ ሀገርን የተረጋጋችና ሰላማዊ በማድረግ ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳለው እንደሚረዱና ለዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነትና ሰላማዊነት የራሳቸውን አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም