ቀጥታ፡

በዞኖቹ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በስፋት በማዘጋጀት የምርት ጥራትንና የአፈር ለምነትን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው

አምቦ፣ ጊምቢ፤ ግንቦት 14/2018(ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ እና በምዕራብ ወለጋ ዞኖች የሰብል ምርታማነትን በዘላቂነት ለማሳደግ እና የአፈርን ለምነት ለመመለስ፣ አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በስፋት አዘጋጅቶ ጥቅም ላይ እንዲያውል እየተደረገ መሆኑን የየዞኖቹ ግብርና ጽሕፈት ቤቶች አስታወቁ።

መንግሥት ከለውጡ ወዲህ ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት የአርሶ አደሩ የማምረት አቅም እያደገ የመጣ ሲሆን፣  አርሶ አደሩ ከፋብሪካ ማዳበሪያ በተጨማሪ በአካባቢው የሚገኙ ጸጋዎችን ተጠቅሞ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲያመርት ሰፊ ሥራ ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል።

በምዕራብ ሸዋ ግብርና ጽሕፈት ቤት የአፈር ልማት ማሻሻያ ቡድን መሪ አቶ ተክሌ ኢዶሳ እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ ከ20 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።

አርሶ አደሮች በአካባቢያቸው ከሚገኙ ቅጠላቅጠሎች፣ ተረፈ ምርቶችና ፍግ በመጠቀም ከእቅድ በላይ 22 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀት ችለዋል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ከባዮጋዝ ዝቃጭ እና ከቨርሚ ኮምፖስት ከ550 ሺህ ኩንታል በላይ ጥራት ያለው ማዳበሪያ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ይህም በድግግሞሽ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የማልማት አቅም እንዳለው ገልጸዋል።


 

በተመሳሳይ በምዕራብ ወለጋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት የአፈር ለምነት ቡድን መሪ አቶ ወንድሙ ኢተፋ እንዳሉት በበጀት ዓመቱ 20 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ለማዘጋጀት ታቅዶ እስካሁን 14 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቷል።

ይህ ኮምፖስት ከ496 ሺህ 317 ሄክታር በላይ መሬት የማልማት አቅም ያለው ሲሆን፣ በአንዳንድ ወረዳዎችም ጥራቱን የጠበቀ ኮምፖስት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የሚያደርጉ የማዘጋጃ ማዕከላት ተከፍተዋል ብለዋል።

ቡድን መሪዎቹ የተፈጥሮ ማዳበሪያው የአፈርን እርጥበትና ለምነት ከመጠበቁም በላይ፣ ቀደም ሲል ምርት መስጠት አቁመው የነበሩ የእርሻ መሬቶችን ዳግም ወደ ለምነታቸው በመመለስ ምርታማነታቸውን እንዲጨምሩ አድርጓል።

በተጨማሪም አርሶ አደሩ ለዘመናዊ የኬሚካል ማዳበሪያ ሊያወጣው የነበረውን ከፍተኛ ወጪ በማዳን ረገድ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ነው ያሉት።

የአምቦ ወረዳ አርሶ አደር መልካሙ ባይሳ እና በሬቻ መንግሥቱ በሰጡት አስተያየት፤ ባለፉት ዓመታት በአካባቢያቸው ከሚገኙ ተረፈ ምርቶች በዓመት እስከ 38 ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እያዘጋጁ መጠቀም መጀመራቸውን ገልጸዋል።

የጊምቢና አይራ ወረዳ አርሶ አደሮች ይማሙ ሌታ እና ቦካ ጅራታ በዚህም የተጎዳው አፈራቸው በማገገሙ የሰብልና ፍራፍሬ ምርታቸው በየዓመቱ እያደገ መምጣቱን አስረድተዋል።
 

በአሁኑ ወቅት የተዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ በከፊል ለበጋ መስኖና ለበልግ እርሻ የዋለ ሲሆን፣ ቀሪውን ለመኸር እርሻ ዝግጅት መሬት ላይ በመበተን ከአፈር ጋር የማዋሃድ ሥራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም