ቀጥታ፡

የምርጫ ካርድ የወሰዱ ዜጎች የመምረጥ መብታቸውን በአግባቡ መጠቀም የሚያስችላቸውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ግንቦት 14/2018(ኢዜአ)፦ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የምርጫ ካርድ የወሰዱ ዜጎች የመምረጥ መብታቸውን በአግባቡ መጠቀም የሚያስችላቸውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሰሩ መሆናቸውን የሲቪል ማህበራት ገለጹ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መራጮች ድምፅ ይሰጡበታል ተብሎ የሚጠበቀው ድምፅ መስጫ ቀን ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውታል።

የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ በተለያዩ ምዕራፎች በማካሄድና በማራዘም ከየካቲት 28 እስከ ሚያዚያ 24 ቀን 2018 ዓ.ም ሲካሄድ ቆይቶ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።

በዲጂታል "ምርጫዬ" መተግበሪያና በየምርጫ ጣቢያዎቹ በአካል በመገኘት የነቃ ተሳትፎ ያደረጉ ሲሆን ከ50 ሚሊየን 514 ሺህ በላይ ዜጎች ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ መውሰድ ችለዋል።

በጠቅላላ ምርጫውም 47 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአጠቃላይ 10 ሺህ 934 ዕጩዎችን በማስመዝገብ በመገናኛ ብዙኅን አማካኝነት የፖሊሲ አማራጭ ሃሳቦቻቸውን ለህዝብ በስፋት በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ።

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለምርጫ ታዛቢነት ዕውቅና የተሰጣቸው 55 የሀገር ውስጥ ድርጅቶችም በተለያዩ አካባቢዎች ከ60 ሺህ 277 በላይ ወኪሎችን አሰማርተዋል።

በመራጮች ትምህርት ላይ ዕውቅና የተሰጣቸው 169 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም ለመራጩ ህዝብ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና ስልጠና እየሰጡ ይገኛሉ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሲቪል ማኅበራት እንዳሉት፤ ድምፅ መስጫ ካርድ የወሰዱ ዜጎች የመምረጥ መመረጥ መብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየሰጡ ነው።

የአዲስ አበባ ሴቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት እናታለም እንዳለ፥ ሀገራዊ ምርጫ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫም በሁሉም ክፍለ ከተሞች የማኅበሩን ከግማሽ ሚሊየን በላይ አባላት በማንቃትና በማስገንዘብ ካርድ እንዲያወጡና በሂደቱም ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም የምርጫ ሂደቱ በስኬት እስኪጠናቀቅ ድረስ የማኅበሩ አባላት ገንቢ ሚናቸውን እንዲወጡ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት በረከት ብርብርሳ በበኩላቸው፤ ወጣቶች ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ የማድረግ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ካርድ የመውሰድ የጊዜ ሰሌዳ ከተጠናቀቀ በኋላም ወጣቶች የተሻለ የፖሊሲ አማራጭ ለሚያቀርብ ድምፅ መስጠት የሚስችል ግንዛቤ እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም ማኅበሩ 2ሺህ በላይ 228 ታዛቢዎችን ከማሰማራት ባሻገር ህብረተሰቡን የማንቃትና የማስገንዝብ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ እያንዳንዱ ዜጋ የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት ማኅበራቱ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም