ለምርጫው ሰላማዊነት እና ዴሞክራሲያዊነት የበኩላችንን እየተወጣን ነው - የባሌ ዞን የሲቪክ ማህበራት - ኢዜአ አማርኛ
ለምርጫው ሰላማዊነት እና ዴሞክራሲያዊነት የበኩላችንን እየተወጣን ነው - የባሌ ዞን የሲቪክ ማህበራት
ሮቤ፣ ግንቦት 14/2018 (ኢዜአ):- 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ መሆናቸውን በባሌ ዞን የሚገኙ የሲቪክ ማህበራት ገለጹ።
ማህበራቱ የምርጫውን ሂደት ለመታዘብና በህብረተሰቡ ውስጥ በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የዞኑ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳ ጣሂር፣ የማህበራቸው አባላት ከማንኛውም ወገንተኝነት በጸዳ መልኩ ሰላምን ለማስጠበቅ እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።
ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ በመፍጠር እና ትክክለኛ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ረገድ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የዞኑ ወጣቶች ማህበር ምክትል ኃላፊ አቶ ጫላ ጌታቸው በበኩላቸው፣ ማህበሩ ለምርጫ ታዛቢዎች ስልጠና መስጠቱን ገልጸዋል።
የማህበሩ አባላት የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ በቁርጠኝነት እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ በታዛቢነት ለተለዩ አባላት የምርጫ ሂደቱን መታዘብ የሚያስችላቸው በቂ ስልጠና ተሰጥቷል ብለዋል።
ወጣቶቹ በስልጠናው ያገኙትን እውቀትና ልምድ ተጠቅመው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ቀጣይነት ያለው ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነም አስረድተዋል።
በምርጫው የሴቶችን ንቁ ተሳትፎ ለማረጋገጥ እየሰሩ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ገነት ካሳሁን ናቸው።
በጠቅላላ ምርጫው ሴቶች የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ በየደረጃው የሚገኙ የማህበሩ አባላት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እየተወጡ ይገኛሉ።
በእውቀት ላይ የተመሰረተ ምርጫ እንዲካሄድ እና የህዝብ ተሳትፎ እንዲጎለብት መረጃዎችን የማድረስ ስራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።
በባሌ ዞን ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በተደራጁ 395 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ፣ ወደ 1 ሺህ የሚጠጉ የሲቪክ ማህበራት አባላት በገለልተኝነት የታዛቢነት ሚናቸውን እንዲወጡ መለየታቸው ታውቋል።