ተገንብቶ ስራ የጀመረው መንገድ የረጅም ጊዜ ጥያቄያችንን የመለሰ ነው-የሰሙሮቢ ወረዳ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ተገንብቶ ስራ የጀመረው መንገድ የረጅም ጊዜ ጥያቄያችንን የመለሰ ነው-የሰሙሮቢ ወረዳ ነዋሪዎች
ሰመራ፣ ግንቦት 14/2018(ኢዜአ)፡- በአፋር ክልል ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው መንገድ የዘመናት የልማት ጥያቄያቸውን በአግባቡ እንደመለሰላቸው የሰሙሮቢ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።
በአፋር ክልል ገቢ እና የኸሪ ራሱ ዞኖችን ለማገናኘት በ433 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የጠጠር መንገድና የድልድይ ፕሮጀክቶች የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባና የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብረሃም በላይ (ዶ/ር) በተገኙበት ተመርቆ ስራ መጀመሩ ይታወሳል።
በመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አማካኝነት የተገነቡት እነዚሁ ፕሮጀክቶች በክልሉ በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች መካከል ያለውን የትራንስፖርት ትስስር ይበልጥ ለማጠናከርና የማህበረሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ታስበው የተገነቡ መሆናቸውም በወቅቱ ተገልጿል።
አሰተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የሰሙሮቢ ወረዳ ነዋሪዎች ባለፉት ዓመታት በአካባቢያቸው ደረጃውን የጠበቀ መንገድ ባለመሰራቱ ምክንያት ማግኘት የሚገባቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ሳያገኙ እንዲቆዩ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወይዘሮ ሀስና ዓሊ መንገዱ በመገንባቱ የዕለት ተዕለት ማህበራዊ ጉዳዮቻችንን በቀላሉ ለመፈጸምና ምርቶቻችንን በወቅቱ ለገበያ ለማቅረብ አስችሎናል` ብለዋል።
ወጣት ኢብራሂም ቡሃዱላ በበኩሉ፤ ቀደም ሲል በነበረው የመንገድ ችግር ምክንያት ከቅርብም ሆነ ከሩቅ ዘመዶቻችን ጋር ለመገናኘትና ማህበራዊ ግዴታዎቻችንን ለመወጣት እንቸገር ነበር በማለት የነበረውን ተግዳሮት አስታውሷል።
የመሰረተ ልማቱ መዘርጋት በአካባቢው ላይ አወንታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉን የጠቀሰው ወጣቱ፤ የመንገዱ አገልግሎት መጀመር ማህበረሰባዊ ትስስርን ከመፍጠሩም ባለፈ በነዋሪዎች ህይወት ላይ ተጨባጭና መልካም ለውጥ ማምጣቱን ተናግሯል።
የሰሙሮቢ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሀሰን መሐመድ በበኩላቸው፤ የተገነባው የመንገድ ፕሮጀክት የአካባቢው ማህበረሰብ ለረጅም ዘመናት በተደጋጋሚ ሲያነሳው የነበረውን የልማት እና የመሰረተ ልማት ጥያቄ በዘላቂነት መመለስ የቻለ መሆኑን አስታውቀዋል።