ቀጥታ፡

በጀጎል መልሶ ማልማት የተሰሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች ሐረር ከተማን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ አድርጓታል

አዲስ አበባ፤ግንቦት 14/2018(ኢዜአ)፦የጀጎል መልሶ ማልማት የኮሪደር ልማት ስራ ከተማዋ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን ከማድረግ ባለፈ ለነዋሪዎች የተመቸች እንድትሆን ያስቻለ መሆኑንም የሀረሪ ክልል ባህል፣ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት በጀጎል አለም አቀፍ ቅርስ ከ22 ኪ.ሜ በላይ የኮሪደር ልማት ስራ መከናወኑን ቢሮው ገልጿል።


 

በክልሉ ባህል፣ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ዳይሬክተር ኢንጅነር አሚር ረመዳን ባለፉት ዓመታት በጀጎል አለም አቀፍ ቅርስ ውስጥ ስለተከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች በሚመለከት መግለጫ ሰጥተዋል።


 

በመግለጫቸውም፥ በክልሉ ባለፉት ዓመታት ቅርሶችን በማልማትና በመንከባከብ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም በማሳደግ ረገድ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።

ከተከናወኑ ተግባራት መካከልም ሺህ ዘመናትን ያስቆጠሩ ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶችን ለጎብኚዎች ምቹና ማራኪ ለማድረግ የተከናወኑ ውጤታማ ሥራዎችን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በክልሉ የሚገኙ ቅርሶችን በመንከባከብና በማልማት ረገድ የተከናወኑ ሥራዎችም ሐረርን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ያደረጉና የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ፍሰትና ገቢ እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

በክልሉ ህዝብን በማሳተፍ ከመንግስት ምንም አይነት በጀት ሳይመደብለት ከ22 ኪሎሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ማልማት መቻሉን ገልጸዋል።


 

ከዚህ በተጨማሪም 3 ነጥብ 4 ኪሎሜትር የሚሸፍነው የጀጎል ግንብ ዙሪያም መልሶ የማልማትና የአረንጓዴ ስፍራ እውን ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በዚህም ከ7 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩንም ነው ኢንጂነር አሚር የተናገሩት።

በአካባቢያዊ ሀብትና እውቀት  የተከናወኑ ስራዎችን በመጠቀም እውን የተደረገው ስራም የቅርሱን ይዘትና ታሪካዊነት ውብ እንዲሆን ማድረግ ስለመቻሉ ገልጸዋል።

በተከናወነው ስራም በገጠርና ከተማ የሚገኘው ህዝብና ተቋማት እንዲሁም ማህበራትና የዲያስፖራ አባላት በኔነት ስሜት ተሳታፊ ሆነዋል ብለዋል።


 

በጀጎል መልሶ ማልማት የተሰሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች ከተማዋ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን ከማድረግ ባለፈ ለነዋሪዎች የተመቸች እንድትሆን ያስቻለ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በቀጣይም የጀጎል አለም አቀፍ ቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም