በክልሉ ለአምራች ኢንዱስትሪው በተሰጠ ትኩረት በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሀብቶች ቁጥር እያደገ መጥቷል - አፈ ጉባኤ ፋንታዬ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለአምራች ኢንዱስትሪው በተሰጠ ትኩረት በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሀብቶች ቁጥር እያደገ መጥቷል - አፈ ጉባኤ ፋንታዬ ከበደ
ሀዋሳ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፡-በሲዳማ ክልል ለአምራች ኢንዱስትሪው በተሰጠ ትኩረት በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሀብቶች ቁጥር እያደገ መምጣቱን የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንታዬ ከበደ ገለጹ።
በሀዋሳ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ዛሬ ተመርቋል።
የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ እንዳሉት እንደ ሀገር በተፈጠረው ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በክልሉ በአምራች ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት ታይቷል።
ለአምራች ኢንዱስትሪው በተሰጠው ልዩ ትኩረትም በክልሉ በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሀብቶች ቁጥር እያደገ መምጣቱ ተናግረዋል።
አምራች ዘርፉ ከፍተኛ የሰው ሃይል የሚፈልግ በመሆኑ የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም አፈ ጉባኤዋ ጠቁመዋል።
ከአነስተኛ ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ማደግ እንደሚቻል አበባ ጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ስፌት አክሲዮን ማህበር ያስገነባው የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ አንድ ማሳያ ነው ብለዋል።
የክልሉ አንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ አሻግሬ ጀምበሩ በበኩላቸው መንግስት አምራች ኢንዱስትሪውን በማበረታታት በርካቶችን ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ የተለያዩ ባለሀብቶች በአምራች ኢንዱስትሪው መስክ እንዲሰማሩ ለማበረታታትም በዘርፉ ለሚሰማሩ መሰረተ ልማት የተሟላላቸው ምቹ ቦታዎችን ማዘጋጀቱንም ተናግረዋል።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ አገና ኔቶ እንዳሉት በከተማዋ ከ1 ሺህ በላይ አነስተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ይገኛሉ።
ኢንዱስትሪዎቹ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩና ለውጪ ገበያ የሚቀርቡትን በማምረት በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
የአበባ ጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ስፌት አክሲዮን ማህበር ሥራ አስኪያጅ ወሌ አበጋዝ (ዶ/ር) በበኩላቸው ለፋብሪካው ግንባታ ከ582 ሚሊዮን በር በላይ ወጪ መደረጉን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው ለ153 ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠሩን ገልጸው፣ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ ለ310 ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በመታገዝ ወደ ኤክስፖርት ምርት መሸጋገራቸውን ጠቁመው፣ ጥራት ያለው ምርት ለማምረትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በፋብሪካው የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች መካከል ወጣት ኤደን ዘርፉ እንዳለችው በፋሽን ዲዛይን ትምህርት መስክ ተመርቃ በፋብሪካው መቀጠሯን ተናግራለች።