ቀጥታ፡

በክልሉ በግብርና እና ገጠር ትራንስፎርሜሽን ወጣቶችን በሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ ላይ የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ

ሀዋሳ፤ ግንቦት 13/2018(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል በግብርና እና ገጠር ትራንስፎርሜሽን ወጣቶችን በሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ ላይ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ገለፀ፡፡

በሲዳማ ክልል የእርሻውን ዘርፍ ለማዘመንና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት በማለም የእርሻ ትራክተሮችን በዘርፉ ለተደራጁ ወጣቶች የማስረከብ መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡


 

በዚህ ወቅት የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ መምሩ ሞኬ እንዳሉት፤ በክልሉ እየተከናወኑ ባሉ የግብርና እና ገጠር ትራንስፎርሜሽን ሥራዎች ወጣቶችን በሥራ ዕድል ተጠቃሚ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል።


 

የግብርና እና ገጠር ትራንፎርሜሽንን ለማረጋገጥ ግቦች ተጥለው ማሳካት የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም የምግብና ሥነ ምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ፣ ለገበያ የማምረት፣ ኤክስፖርትን የማሳደግና ገቢ ምርትን የመተካት እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ የግብርና ምርቶችን በስፋት የማምረት ግቦች እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡

በግብርና ዘርፍ ለተደራጁ ወጣቶች የእርሻ ትራክተሮች ርክክብ መከናወኑን ገልፀው በዚህም በአጠቃላይ 148 ወጣቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስረድተዋል፡፡

የአካታችና ዘላቂ የግብርና እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት ብሔራዊ አስተባባሪ ሰለሞን ዳኜ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በገጠር በተለይ ወጣቶችና ሴቶችን አደራጅቶ ተሳታፊ በማድረግ የገጠሩን ኢኮኖሚ የማሳደግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም ምርትና ምርታማነትን በማስፋትና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት በኩል ፕሮጀክቱ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

ትራክተሮቹን ከተረከቡ ማህበራት መካከል የቦና ወረዳ ወጣት ንግስት አምሳለ ማህበራቸው በቆሎ፣ ስንዴ እንዲሁም አቮካዶ፣ ማንጎና ሌሎች የተለያዩ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ፍራፍሬዎችን እንደሚያመርት ገልፃለች፡፡

ከዚህ ቀደም የግብርና ሥራውን ባህላዊ በሆነ መንገድ ስለሚያከናውኑ ውጤታማነታቸው እምብዛም እንደነበር ገልፃ አሁን ላይ ሰፊ መሬትን በትራክተር በተሻለ ሁኔታ በማረስ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸውን ዕድል እንዳገኙ ተናግራለች፡፡

የዳራ ወረዳ ወጣት አዲሱ ሌላሞ በበኩሉ ማህበራቸውም ሆነ በአካባቢያቸው ያሉ አርሶ አደሮች በበሬ አልያም በጉልበት የእርሻ ሥራቸውን እንደሚያከናውኑ ተናግሯል፡፡

ትራክተሮቹን የራሳቸውን እንዲሁም በአካባቢያቸው ያሉ አርሶ አደሮችን ማሳ ለማረስ እንደሚጠቀሙባቸው ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም