ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልፅግና በልጆቿ ጥረት ዕውን ማድረግ እንደሚቻል የገላን ኢንዱስትሪ ፓርክ ህያው ምስክር ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልፅግና በልጆቿ ጥረት ዕውን ማድረግ እንደሚቻል የገላን ኢንዱስትሪ ፓርክ ህያው ምስክር መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኩን የጎበኙ የመዲናዋ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ግንቦት 8 ቀን 2018 የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክን መርቀው ሥራ ማስጀመራቸው ይታወቃል።

ከአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የማህበረሰብ ክፍሎችም የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ የልማት ውጤትና የአምራቾችን የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።


 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የተጠሪ ተቋማት ዘርፍ ኃላፊ ዳዲ ወዳጆ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኢንዱስትሪ ክላስተር መሆኑን ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኩም የአምራቾችን ዓለም አቀፍ የተወዳዳሪነት አቅም በመገንባት ሀገራዊ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ገንቢ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

ለዚህም ፓርኩ የአዲስ አበባና የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ የሚያፋጥን የኢንዱስትሪ ምርታማነትን ምኅዳር እንደፈጠረ አንስተዋል።

አዲስ አበባ በሁሉም ዘርፍ ስኬታማና ውጤታማ የልማት ሥራዎችን ዕውን የምታደርግ ከተማ መሆኗን የገላን ኢንዱስትሪ ፓርክ እንደሚያሳይ አስረድተዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኩም ለመካከለኛና ከፍተኛ አምራቾች ምቹ የሥራ ከባቢ በመፍጠር በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በተኪና ወጪ ንግድ የምርት አቅም መገንባት የሚያስችላቸው መሆኑን አብራርተዋል።


 

ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የመጣው አብዱራሂም አስገዶም፤ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ኢትዮጵያዊያን መስራትና ለውጥን ማምጣት እንደሚችሉ የሚያሳይ አስደናቂ የልማት ውጤት ነው ብሏል።

የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልፅግና በልጆቿ ጥረት ዕውን ማድረግ እንደሚቻል የገላን ኢንዱስትሪ ፓርክ ህያው ምስክር መሆኑን ተናግሯል።


 

ሌላኛው ከለሚኩራ የመጣው አስቻለው ሙሉጌታ በበኩሉ፤ የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ አምራቾች የሚገጥማቸውን የመስሪያ ቦታ ችግር የሚቀርፍ የልማት አቅም መሆኑን ገልጿል።

የጉለሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪዋ የጉብኝቱ ተሳታፊ ፍጹም አምሳሉ፤ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ለሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት አቅም የሚሆን የማምረቻ ከባቢ መሆኑን ተናግራለች።


 

የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ በርካታ የመዲናዋ ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ አስደናቂ ፕሮጀክት ነው ያለው ደግሞ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ የመጣው ዮኃንስ ሰለሞን ነው።


 

ፓርኩም የተኪ ምርታማነትን በማሳደግ ለሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ገበያ መቅረብ የሚችሉ የኢንዱስትሪ ምርቶችን የማምረት አቅም እንደሚያጎለብት ማየቱን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም