ቀጥታ፡

መንግስት ለህዝብ የገባውን ቃል ይፈፅማል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦ መንግስት ለህዝብ የማይሰራውን ቃል አይገባም፤ ለህዝብ የገባውን ቃል ይፈፅማል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ዛሬም የኑሮ ውድነትን ለማቃለል፣ ምርት በብዛት ማቅረቢያ እና የግብይት ማዕከላት የማስፋት ስራችን አካል የሆነው 7ኛውን የለሚ ሁለገብ የገበያ ማዕከልን ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል ብለዋል።


 

ማዕከሉ የኑሮ ውድነትን የሚያቃልሉ ዘመናዊ፣ ማሞቂያ እና ማቀዝቀዣ ያላቸው 221 መጋዘኞች፥ የችርቻሮ ሱቆች፥ ሱፐር ማርኬቶች፣ ወፍጮ ቤቶች፣ በአንድ ጊዜ 250 ተሽከርካሪዎችን ማቆም የሚችል ፓርኪንግ፣ ለለሚ ኩራ፣ ለቦሌ እና የካ ክፍለ ከተሞች ነዋሪዎች በአማካይ ቦታ እና ሰሚት ዋና መንገድ ላይ የሚገኝ ምቹ የሆነ ሁለገብ የገበያ ማዕከል ነው ብለዋል።

በገበያ ማዕከሉ ማህበረሰቡ ለዕለት ፍጆታ የሚጠቀምባቸውን የሰብል ምርቶች፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች፣ የበርበሬ ፣የቅመማቅመም ምርቶች እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን የአንድ ማዕከል የግብይት ስርዓትን እውን ማድረግ መቻሉን ነው ከንቲባዋ የገለጹት።

በማዕከሉ የሚቀርቡ ምርቶች ከ15 እስከ 20 በመቶ የዋጋ ቅናሽ የሚሸጥበት፥ ዋጋ የሚያንረውን ህገ-ወጥ የደላላ ሰንሰለት በመበጣጠስ ከአምራቹ ያልተቋረጠ ምርት የሚቀርብበትና የከተማዋ ነዋሪዎችን የኑሮ ጫና እንደሚያቃልል አመልክተዋል።


 

በገበያ ማዕከሉ ከተለያየ ቦታ በኮሪደር ልማት የተነሱ ነዋሪዎችን ጨምሮ ማዕከሉ ያረፈበትን 3 ነጥብ 2 ሄክታር መሬት ለልማት የለቀቁ አርሶ አደሮችም ሱቅ እንዲያገኙ መደረጉንና በዚህም ለነዋሪዎች ሰፊ የስራ እድል መፈጠሩን ተናግረዋል።

ለህዝብ የገባነውን ቃል በተግባር እንዲሳካ ጥረት ላደረጉ የዲዛይንና የኮንስትሪክሽን ስራዎች ቢሮ አመራርና ሰራተኞች፣ የንግድ ቢሮ አመራሮችና ሰራተኞች፣ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አመራሮች፣ ቦታው ለልማት እንዲውል ለሰጣችሁ አርሶ አደሮች በራሴና እና በከተማ አስተዳደሩ ስም አመሰግናለሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም