መንግስት የአፈር ማዳበሪያን በሀገር ውስጥ ለማምረት የጀመረው ጥረት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ የልማት አቅም ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የአፈር ማዳበሪያን በሀገር ውስጥ ለማምረት የጀመረው ጥረት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ የልማት አቅም ነው
ድሬዳዋ፤ ግንቦት 13/2018(ኢዜአ)፦ መንግስት የአፈር ማዳበሪያን በሀገር ውስጥ ለማምረት የጀመረው ጥረት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ የልማት አቅም መሆኑን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ከተረጂነት ወደ ምርታማነት" በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የፓናል ውይይት በድሬዳዋ ተካሂዷል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት የዜጎችን ክብርና የሀገርን ሉዓላዊነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ አበረታች ስራዎች እየተሰሩ ነው።
ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር በተጀመሩ ኢንሼቲቮች በሚሊየን የሚቆጠሩ ቤተሰቦችን ከልማታዊ ሴፍቲኔት በመላቀቅ ወደ አምራችነት ተሸጋግረዋል ብለዋል።
እንዲሁም ከራሳቸው አልፈው ለብሔራዊ የእህል ክምችት አበርክቷቸው መጨመሩን ገልጸው እነዚህን ስራዎች በላቀ ደረጃ በማሳካት የሀገርና የዜጎችን ክብር ለመመለስ የተጀመረው የማዳበሪያ ፋብሪካ ወሳኝ እመርታ መሆኑንም አመልክተዋል።
የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ዑመር በበኩላቸው በክልሉ የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶች አምጥተዋል።
በተለይ ከሃረማያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለአርሶ አደሮች የተሰጡ ድጋፎችና ክትትሎች ምርታማነትን በማሳደግ በኩል ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ነው ያሉት።
በሶማሌ ክልል የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ ግብርናና ምግብ ዋስትና ዳይሬክተር ከድር መሐመድ በበኩላቸው ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ተከትሎ የገፀ እና ከርሰ ምድር ሃብቶችን በአግባቡ በመጠቀም አርሶ እና አርብቶ አደሮችን ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር አበረታች ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
በዚህም ክልሉ ያለው ሰፊ የውሃ እና የእርሻ መሬት እንዲሁም የእንስሳት ሃብት ዜጎችን ከተረጂነት ለማላቀቅ እየዋሉ መሆኑን ገልጸዋል።
የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ልማትና ሌሎች የልማት ስራዎች አርብቶና አርሶ አደሩን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የማሸጋገሩን ጉዞ ስኬታማ ማድረጋቸውን የገለፁት ደግሞ በአፋር ክልል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የግብርናና ምግብ ዋስትና ከፍተኛ አስተባባሪ ከዲር ኢብራሂም ናቸው።
ኢዜአ እና ግብርና ሚኒስቴር በጋራ ያዘጋጁት ሀገር አቀፍ የፓናል ውይይት በቀጣይ የተሻለ እና የተቀናጀ ስራ ለመስራት ያስችላል ብለዋል።