የመዲናዋ የልማት ሥራዎች የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረጉ ናቸው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የመዲናዋ የልማት ሥራዎች የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረጉ ናቸው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረጉ መሆናቸውን የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የተገነባውን ሰባተኛውን የለሚ ሁለገብ የገበያ ማዕከል መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
ከንቲባዋ በዚሁ ጊዜ፤ በአዲስ አበባ የሚገነቡ ማንኛውም የልማት ሥራዎች የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ተጨባጭ ውጤት የሚያስገኙ ናቸው ብለዋል።
በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ የመዲናዋን ነዋሪዎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስቻሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ የልማት ስኬትም ነዋሪዎችና ባለሃብቶች ባደረጉት የዕውቀት፣ የጉልበትና የገንዘብ ድጋፍና ትብብር የመጣ መሆኑንም ተናግረዋል።
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የገበያ ማዕከልም ምርትና አገልግሎቶችን በብዛትና በጥራት በማቅረብ የገበያ መረጋጋትን የሚፈጥር ወሳኝ መሰረተ ልማት ነው ብለዋል።
ይህም የነዋሪዎችን የኑሮ ጫና በማቃለል ምርትን በብዛትና በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ እንደሚያስችል ጠቅሰዋል።
ማዕከሉ ምርቶችን በቀጥታ ከእርሻ እንዲገቡ በማድረግ አላስፈላጊ የምርት ብክነትን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ያስችላል ብለዋል።
ማዕከሉ የጥራጥሬ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የቅባት እህሎችና ሌሎች መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን በጥራት ማቅረብ የሚያስችል ዘመናዊ መሰረተ ልማት የተሟላለት መሆኑንም ተናግረዋል።