የኢትዮጵያን የዲጂታል ሉዓላዊነት በማረጋገጥ የሳይበር ደኅንነት ስጋትን የሚቀለብስ የሰው ሃይል ማፍራት እየተቻለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የዲጂታል ሉዓላዊነት በማረጋገጥ የሳይበር ደኅንነት ስጋትን የሚቀለብስ የሰው ሃይል ማፍራት እየተቻለ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የዲጂታል ሉዓላዊነት በማረጋገጥ የሳይበር ደኅንነት ስጋትን የሚቀለብስ የሰው ሃይል ማፍራት እየተቻለ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ገለጸ።
አስተዳደሩ በዘንድሮው ክረምት ለ5ኛ ጊዜ የሚያካሂደውን የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ (Cyber Talent Summer Camp) ዝግጅት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የአስተዳደሩ የሳይበር ልህቀት ማዕከል ዳይሬክተር ቢሻው በየነ በመግለጫቸው፤ መርሃ ግብሩ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች በማሰልጠን የሳይበር ደኅንነትና የቴክኖሎጂ ሙያተኞችን ለማፍራት ያለመ ነው ብለዋል።
የስልጠና መርሃ ግብሩ የኢትዮጵያን የሳይበር ደኅንነትና ሉዓላዊነት የማስጠበቅ አቅምን የበለጠ ለማጠናከር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።
የመርሃ ግብሩ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ በዘርፉ ሀገራቸውን ከሳይበር ጥቃት የሚከላከልና ብቁ የሳይበር ሠራዊት ማፍራት መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ እስራኤል፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ ያሉ ሀገራት ተሞክሮ መርሀግብሩ ታዳጊዎችን ለማፍራት ያለውን ወሳኝነት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
ይህ ካምፕ የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂን ስኬታማ ለማድረግና የኢትዮጵያን ዲጂታል ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።
የዘንድሮው የስልጠና ካምፕ በክልል ደረጃ በስድስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲካሄድ የተወሰነ ሲሆን ይህም ታዳጊዎች በቅርበት ስልጠናውን እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በእስካሁኑ ሂደትም ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ ከ4 ሺህ በላይ ታዳጊዎችና ወጣቶች መመዝገባቸውን ገልፀዋል።
ምዝገባውም ግንቦት 17/2018 ዓ.ም የሚጠናቀቅ በመሆኑ በሳይበር ደህንነትና ቴክኖሎጂ ልዩ ተሰጥኦና ፍላጎት ያላቸው ታዳጊዎችና ወጣቶች በኦንላይን እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርበዋል።