በክልሉ ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ይበልጥ ለማስፋፋት የተቀናጁ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ይበልጥ ለማስፋፋት የተቀናጁ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው
ጅግጅጋ፤ ግንቦት 13/2018(ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል ጥራት ያለውና ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ይበልጥ ለማሳደግ ዘላቂ ስራዎች በልዩ ትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ኡስማን ገለጹ።
የሶማሌ ክልል ጤና ቢሮ 1ኛውን ዓመታዊ የጤና አገልግሎት ጥራት እና ኢኖቬሽን ጉባኤ በጅግጅጋ ከተማ እያካሄደ ነው።
የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ኡስማን በጉባኤው ባደረጉት ንግግር መንግስት ቀልጣፋ አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ ከፍተኛ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል።
ከለውጡ በኋላ በክልሉ አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ተቋማትን ተደራሽነት ለማስፋፋት፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራትና የሕክምና ግብዓቶችን ለማሟላት ሰፊ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም የጤና አገልግሎቱን በዲጂታል ሥርዓት በመደገፍ፥ ለኅብረተሰቡ ቀልጣፋ፣ ምቹና ተደራሽ በሆነ መንገድ ለመስጠት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በመድረኩ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ እንደገለጹት ከለውጡ በኋላ መንግስት ለክልሉ የሠጠው ትኩረት በርካታ ስኬቶች እንዲመዘገቡ አስችሏል።
የጤናውን ዘርፍ በግብዓትና በሰለጠነ የሰው ሀይል በማሟላት ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት በተለይም በአርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ ዘንድ ተደራሽ እንዲሆን ከፍተኛ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
የሶማሌ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሴ አህመድ በበኩላቸው፤ የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ በማድረግ ተቋማቱ ለኅብረተሰቡ ምቹና ጥራት ያለው እንክብካቤ መስጠት እንዲችሉ ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በእናቶችና ሕፃናት ጤና አጠባበቅ በኩል ከፍተኛ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው፤ ከለውጡ ወዲህ በክልሉ ስድስት የኦክስጂን ማምረቻ ማዕከላት መገንባታቸውንና ከእነዚህም መካከል ወደ ሥራ የገቡ መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ለአብነትም በ240 ሚሊየን ብር ወጪ በካራማራ አጠቃላይ ሆስፒታል የተገነባው የፌስቱላ ማዕከልና የኦክስጂን ማምረቻ ማዕከል ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ተናግረዋል።
የአሁኑ ጉባኤም ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ሊያሳድጉ የሚችሉ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች፣ የመድኃኒትና የሕክምና ግበዓቶች አቅርቦቶች፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች እንዲሁም የልምድ ልውውጦች የሚቀርቡበት መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል።
ለሁለት ቀናት በተሰናዳው ጉባዔ የፌዴራልና የክልል የዘርፉ አመራሮች እና የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ተወካዮች እየተሳተፉ ናቸው።