ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ወሳኝ ድል ተቀዳጅቷል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ33ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ሲዳማ ቡና አርባምንጭ ከተማን 3 ለ 0 አሸንፏል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ መስፍን ታፈሰ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር የአርባምንጭ ከተማው ኤፍሬም ታምራት በራሱ ላይ ቀሪዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።

በ14 ጎሎች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የሚመራው የሲዳማ ቡናው አጥቂ አቤል ያለው ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት ወደ ህክምና ስፍራ ተወስዷል።

ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ሲዳማ ቡና በ58 ነጥብ መሪነቱን አጠናክሯል። ከተከታዩ መቻል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ከፍ አድርጓል።

በሊጉም 16ኛ ድሉን አስመዝግቧል።

በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ 14ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው አርባምንጭ ከተማ በ29 ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃ ይዟል። ቡድኑ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ድል አልቀናውም።




በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ሌላኛው መርሐ ግብር አዳማ ከተማ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

ውጤቱን ተከትሎ አዳማ ከተማ በ39 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ድል አልቀናውም።

ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ40 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በ33ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር ነገሌ አርሲ ከምድረ ገነት ሽሬ ምሽት 12 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም