የምርት ጥራት ደረጃ ማረጋገጫ መተግበሪያው የኢትዮጵያን የንግድ ስርዓት ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምርት ጥራት ደረጃ ማረጋገጫ መተግበሪያው የኢትዮጵያን የንግድ ስርዓት ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2018(ኢዜአ)፦ የምርት ጥራት ደረጃ ማረጋገጫ መተግበሪያው የኢትዮጵያን የንግድ ስርዓት አፈጻጸም ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት በዛሬው ዕለት የምርት ጥራት ደረጃን በኦንላይን ማረጋገጥ የሚያስችል መተግበሪያ አስመርቆ ወደ ስራ አስገብቷል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሠረት በቀለ (ዶ/ር) ተገኝተዋል፡፡
ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ በንግድ ስርዓቱ ላይ ትልቅ እመርታ እንዲመዘገብ አድርጓል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከ46 በላይ አገልግሎቶች በኦንላይን እየተሰጡ እንደሚገኙ ጠቅሰው፥ ይህም የንግድ ሥርዓቱን በማዘመን የምርት ጥራት አፈፃጸም ላይ የላቀ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻሉን ገልጸዋል።
በ2018 በጀት ዓመት አስር ወራት ብቻ ከወጪ ንግድ ከ8 ነጥብ 7 ቢሊየን በላይ የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱንም ነው የተናገሩት፡፡
ዛሬ የተመረቀው የኦንላይን መተግበሪያ አገልግሎቶችንና የምርት ጥራትን በላቀ አፈፃጸም መምራት የሚያስችል መሆኑንና የኢትዮጵያን የንግድ ስርዓት አፈፃጸም ውጤታማነት ለማላቅ አይነተኛ ሚና ያበረክታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሠረት በቀለ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ተስፋ ሰጭ የለውጥ ጉዞ እያስመዘገበች ትገኛለች ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ የለውጥ ጉዞውን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሕግና ተቋማዊ ማሻሻያዎችን እንዳደረገ በመግለጽ፡፡
የዚህ ጥረት አካል የሆነው የኦንላይን የምርት ጥራት ማረጋገጫ መተግበሪያ የኢትዮጵያ ምርቶችን በዓለም አቀፍ ገበያ በዋጋና በጥራት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑንም አክለዋል፡፡
መተግበሪያው የኢንስቲትዩቱን የማስፈጸም አቅም ሀገሪቱ ከደረሰችበት የዕድገት ደረጃ ጋር እንዲጣጣም አጋዥ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በምርት ጥራት ላይ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራት ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ እንደሚሆኑ የተናገሩት ደግሞ የአፍሪካ የደረጃዎች ተቋማት የማዕከላዊ ኮሚቴ ጸሐፊ ሬዩበን ጊሶር ናቸው፡፡
ኢንስቲትዩቱ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ያከናወናቸውን አጠቃላይ ተቋማዊ የሪፎርም ስራዎችን አስመርቋል።