ቀጥታ፡

ከተረጂነት ለመውጣት በተተገበሩ ኢንሼቲቮች የራስን ችግር በራስ መፍታት እንደሚቻል ማሳየት ተችሏል

ድሬደዋ፤ ግንቦት 13/2018(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ከተረጂነት ለመውጣት በተተገበሩ የተሳኩ ኢንሼቲቮች የራስን ችግር በራስ አቅም መፍታት እንደሚቻል በተግባር ማሳየት መቻሉን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት" የሚል መሪ ሃሳብ ያለው የውይይት መድረክ በድሬዳዋ ከተማ ተካሂዷል።


 

ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ በመድረኩ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ እየተተገበረ የሚገኘው ከተረጂነት ለመውጣት ያለመው መርሃ ግብር ተጨባጭና ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል።

ከሁሉም በላይ አጀንዳው በተግባር መሬት መውረዱና በአመራሩ እና በህዝቡ ዘንድ ጠንክሮ ከተሰራ ከተረጂነት መውጣት እንደሚቻል ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል ብለዋል።

በየደረጃው የሚገኘው አመራር በአካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ጸጋና አቅም በመለየት፣ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት እንቅስቃሴዎችን መጀመሩን ጠቅሰዋል።

ከተረጂነት ለመውጣት የሚደረገው እያንዳንዱ ጥረት ከመንግስት የልማት ፕሮጀክቶች እና ዋና ዋና ኢንሼቲቮች ጋር ተናቦ መተግበሩ ለአጀንዳው ስኬታማነት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ገልፀዋል።

በየአካባቢው ከተረጂነት መውጫ የትኩረት አቅጣጫዎችን ለይቶ ስልጠና መስጠት መቻሉና የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራምን ከአካባቢ ልማት ጋር ማስተሳሰር መቻሉ ውጤታማ አድርጎታል ነው ያሉት።

ባለፉት ዓመታት በተሰሩ የተቀናጁ ስራዎች የሚከሰቱ ችግሮች በህዝብ ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ስጋቶች መቀነስ ተችሏል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህም በበርካታ ተጋላጭ ወረዳዎች ላይ በተግባር መረጋገጡን አንስተዋል።

በዚህም መሠረት በርካታ ዜጎች ከተረጂነት ወጥተው፣ ትርፍ አምራች በመሆን ሀብት ማፍራት የጀመሩ ሲሆን፤ ከራሳቸው ፍጆታ አልፈው ለሌሎች መትረፍ የቻሉበት ደረጃ ላይ መደረሱን አብራርተዋል።

ከእንስሳት ሀብት ልማት አንጻርም በተሻለ ሁኔታ ውጤታማ የሆኑ በርካታ የአርብቶ አደር አካባቢዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ለሌሎች አካባቢዎች የእንስሳት መኖ ማቅረብ የጀመሩ መኖራቸውን በአብነት አንስተዋል።

በአጠቃላይ በመርሃ ግብሩ የተከናወኑ ስራዎች ኢትዮጵያ የራስን ችግር በራስ የመፍታት አቅም እንዳላት በተግባር ያረጋገጠችበት ታሪካዊ ጉዞ መሆኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

በመርሃ ግብሩ አማካኝነት በገጠር አካባቢዎች የመሰረተ ልማት ተደራሽነትን በሰፊው ማስፋፋት መቻሉ፣ በተለይም የሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንዲያድግ ተደርጓል ብለዋል።

በዚህም ህብረተሰቡ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን የመቋቋም አቅሙ ጎልብቷል ነው ያሉት።

በተሰሩ ስራዎች አደጋዎችን መቋቋም ተጀምሯል፤ ኢትዮጵያም የራሷን ችግር በራሷ መፍታት እንደምትችል ለዓለም ማሳየት ጀምራለች ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም