ኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋትን በመቀነስ የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ማጠናከር የሚያስችል ውጤት እያስመዘገበች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋትን በመቀነስ የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ማጠናከር የሚያስችል ውጤት እያስመዘገበች ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋትን በራስ አቅም ምላሽ በመስጠት የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ማጠናከር የሚያስችል ውጤት እያስመዘገበች መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ገለጹ።
የአፍሪካ መሪዎች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸደቀውንና እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር ከ2015 ጀምሮ ለ15 ዓመታት የሚቆየውን የሰንዳይ ማዕቀፍ ተከትሎ አባል ሀገራት በየሁለት ዓመቱ የአደጋ ሥጋት ቅነሳ ግምገማ እንዲካሄድ ውሳኔ አሳልፈዋል።
በዛሬው ዕለትም 4ኛው ዙር የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት የአደጋ ሥጋት ቅነሳ ግምገማ በሕብረቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ መካሄድ ጀምሯል።
የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) በዚህ ወቅት፤ የአፍሪካ ሀገራት አደጋዎች እያስተናገዱ ቢሆንም የዓለም አቀፍ አጋርነት እያሽቆለቆለ ነው ብለዋል።
የአህጉሪቱን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ተጋላጭነት ለመቀነስም በአባል ሀገራት መካከል የአደጋ ሥጋት ቅነሳ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ትብብር መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነት ፍኖተ ካርታና ፓኬጅ በመቅረፅ ድጋፍ የሚስፈልጋቸውን የመለየትና የመደገፍ ሥራ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።
የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ተጋላጭነትን በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የእሳትና ቅፅበታዊ አደጋዎች ደንብን በማፅደቅ ጭምር እየተሰራበት መሆኑን አንስተዋል።
የስትራቴጂክ መጠባበቂያ ክምችት አቅምን በማጎልበት ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ምላሽ መስጠት የሚያስችል አስተማማኝ አቅም እየተፈጠረ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
የተረጂነት ባህልና አስተሳሰብን ለመቀየርም በቤተሰብና በማህበረሰብ ደረጃ የአምራችነትን ባህል ማጎልበት የሚያስችል ግንዛቤ እያደገ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም በአፍሪካ የአደጋ ሥጋት ተፅዕኖ ቅነሳ ማዕቀፍ ስር በፖሊሲና ስትራቴጂክ አሰራር የሚመራ ተምሳሌታዊ ውጤት እየተገኘ መሆኑን አስረድተዋል።
በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የዘላቂ አካባቢና ብሉ ኢኮኖሚ ዳይሬክተር ሀርሰን ንያምቤ በበኩላቸው፤ በአፍሪካ የአደጋ ሥጋት ቅነሳ ግምገማ የሞት መጠን እየቀነሰ መጥቷል ብለዋል።
የአህጉሪቱን የአደጋ ሥጋት በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠትም አሕጉራዊ የአደጋ ምላሽ ፈንድ በማቋቋም በትብብር መስራት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የዓለምአቀፍ አጋሮች የአፍሪካን የአደጋ ሥጋት የመረዳት ፍላጎት እየቀነሰ በመምጣቱ ትብብርን የሚያጠናክር ፖሊሲና ተቋማዊ አቅም በመገንባት በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።