ፓርቲው በሁለንተናዊ የልማት ተግባራት ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ፓርቲው በሁለንተናዊ የልማት ተግባራት ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ አድርጓል
ግንቦት 13/2018(ኢዜአ)፦ ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት ባከናወናቸው ሁለንተናዊ የልማት ተግባራት ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረጉን የገንዳውኃ፣ ሰቆጣ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃንና ኮምበልቻ ከተሞች አስተያየታቸውን የሰጡ ሴቶችና ወጣቶች ገለጹ።
በገንዳውኃ፣ ሰቆጣ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃንና ኮምቦልቻ ከተሞች “ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር!" በሚል መሪ ሐሳብ የቅስቀሳና ድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።
በገንዳ ውሃ ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ከተሳተፉት መካከል ወይዘሮ የምስራች አበበ እንዳሉት፤ ፓርቲው ሴቶች ተደራጅተው መብትና ጥቅማቸውን እንዲያስጠብቁ አድርጓል ብለዋል።
ሴቶችን ወደ አመራር በማምጣት፣ በተለያዩ ገቢ ማስገኛ ስራዎች እንዲሰማሩ በመደገፍና በልማት ስራዎች በማሳተፍ ኑሯቸውን እንዲቀይሩ ማድረጉን ገልጸዋል።
ሌላዋ የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊ ቤዛዊት አስናቀው ኢትዮጵያን በምግብ ራሷን በማስቻል ወደ ተሻለ እድገት ለማሻገር የተሰራው ስራ ፍሬ ማፍራቱን ጠቁመዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የገንዳውኃ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አስማረች ቆያቸው ፓርቲው የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሰቆጣ ከተማ በተካሄደው ሰልፍ ላይ የተገኙት የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ፋንታይቱ ካሴ እንደገለጹት ብልፅግና የህብረ ብሔራዊ አንድነትና የአብሮነት ተምሳሌት ነው ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ ወይዘሮ ላቀች ሰማ እንዳሉት መንግስት ባለፉት ዓመታት ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኝነት ሰርቷል።
በቀጣይም ሴቶችን በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች የላቀ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ወይዘሮ ሰላም ተመስገን እና ወይዘሮ እመቤት አንዷለም እንዳሉት ፓርቲው የያዘውን ራእይ ለማሳካት የድርሻችን እንወጣለን ብለዋል።
እንዲሁም በደብረ ብርሃን ከተማ የድጋፍ ሰልፍ ተሳታፊ የሆኑት ወይዘሮ አባይነሽ ሃይሉና ወይዘሮ ረድኤት በሻው እንደገለጹት ፓርቲው የጀመራቸውን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደትን ከዳር ለማድረስ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ ኃላፊ ወይዘሮ ዓለም መኩሪያ እንደገለጹት ፓርቲው ሴቶችና ወጣቶችን በማሳተፍ እየሰራ ይገኛል።
በፓርቲው የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሙሉጌታ አቢ በከተማዋ በተካሄደው ሰልፍ ላይ እንደገለጹት ፓርቲው የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ መጪውን ትውልድ ለመገንባት አልሞ እየሰራ ይገኛል።