ኢንስቲትዩቱ አዳዲስ ተመራማሪዎችን እና የጤና ባለሙያዎችን በማሰልጠን ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
ኢንስቲትዩቱ አዳዲስ ተመራማሪዎችን እና የጤና ባለሙያዎችን በማሰልጠን ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦ አርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ምርመራን ከማሻሻል ባለፈ አዳዲስ ተመራማሪዎችን እና የጤና ባለሙያዎችን በማሰልጠን ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ገለጹ።
ኢንስቲትዩቱ በሕክምናው ዘርፍ በወባ በሽታ ላይ የላቀ የምርምር ሥራ ያከናወኑ ለሦስት ወጣት ተመራማሪዎች የ23ኛውን «ቶሬ ጎዳል» የሳይንስ እውቅና ሽልማት ዛሬ ሰጥቷል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ዓመታት እንደ ቲቢ፣ ወባ፣ ኤች.አይ.ቪ፣ ሄፓታይተስ፣ ኮሌራ፣ ኒሞኒያ እና ማጅራት ገትር በካንሰር እና በተለያዩ በሽታዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሰፊ ምርምር ሲያደርግ ቆይቷል።
እንዲሁም በጤና ፈጠራዎች፣ በክሊኒካዊ ሙከራዎች፣ በክትባት ምርምር፣ በባህላዊ ሕክምና እና በፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ዙሪያ ግንባር ቀደም ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ የበሽታዎችን መከላከል፣ መቆጣጠር እና ምርመራን ከማሻሻል ባለፈ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር አዳዲስ ተመራማሪዎችን እና የጤና ባለሙያዎችን በማሰልጠን ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ጨምረው አስታውቀዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር) የተመረቀው አዲሱ የምርምር ማዕከል እና ተያያዥ ፋሲሊቲዎች ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ ያላቸው ትልቅ ሀብቶች መሆናቸውን አንስተው ለዚህ ስኬት ትልቅ አቅም እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
በሕክምናው ዘርፍ ከፍተኛና ውጤታማ የምርምር ሥራዎችን በማከናወን የ"ቶሬ ጎዳል" ሽልማትን ያገኙት ተሸላሚዎች በሙሉ የተሰማቸውን ኩራት ገልጸዋል፡፡
የዕለቱ ሽልማትም ለሀገር የሚጠቅም ምርምር የሚያደርጉ ወጣት ተመራማሪዎች እንዲወጡ ትልቅ አቅም እንደሚሆንም ጨምረው አስታውቀዋል።
ሽልማቱን የተቀበሉት ወጣት ተመራማሪዎች በበኩላቸው የተበረከተላቸው እውቅና ለቀጣይ የምርምር ሥራዎቻቸው ትልቅ ጉልበትና መነሳሳት እንደሚሆናቸው ገልጸው፤ በቀጣይም በሕክምናው ዘርፍ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
ዘንድሮ ለ23ኛ ጊዜ በተካሄደው በዚህ የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ የመንግሥት ተቋማት፣ ኤምባሲዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በኖርዌያዊው የሕክምና ሳይንቲስት ፕሮፌሰር ቶሬ ጎዳል የተሰየመው ይህ ሽልማት በኢትዮጵያ በጤና ምርምር ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ወጣት ተመራማሪዎች ይበረከታል፡፡