ቀጥታ፡

በክልሉ የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን ለማሳደግ እየተከናወኑ ባሉ የልማት ስራዎች ላይ፣ የአጋር አካላት ሚና የጎላ ነው

አሶሳ፤ ግንቦት 13/2018(ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን ለማሳደግ እየተከናወኑ ባሉ የልማት ስራዎች ላይ፣ የአጋር አካላት ሚና የጎላ መሆኑን የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ መንጌ ወረዳ ፋሮ ፋውንደሽን የተሰኘ ድርጅት ያስገነባው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።


 

በዕለቱ የተገኙት የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ሀጂራ ኢብራሂም እንደተናገሩት፤ የህብረተሰቡን የንፁህ መጠጥ ውሃ ጥያቄ ለመመለስ በመንግስት በኩል እየተከናወኑ ከሚገኙ ስራዎች በተጨማሪ የአጋር ድርጅቶች ዕገዛ ከፍተኛ ነው።

በመንጌ ወረዳ የተገነባው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትም የህብረተሰቡን የንፁህ መጠጥ ውሃ ጥያቄ የመለሰ እና ህብረተሰቡ በንፁህ መጠጥ ውሃ ፍለጋ ሲደርስበት የነበረውን ድካም እና እንግልት ያስቀረ ነው ብለዋል።


 

ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ በፀሐይ ሃይል የሚሰራ በመሆኑ ከአከባቢው የአየር ሁኔታ ጋር የሚጣጣም እና የረጂም ጊዜ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የፋሮ ፋውንደሽን ከፍተኛ የኮንስትራክሽን ባለሙያ ኢንጂነር ሀብታሙ ሀይሌ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ በክልሉ በትምህርት፣ በጤናና ንፁህ የመጠጥ ውሃ ግንባታዎችን በማከናወን የህብረተሰቡን ችግር በማቃለል ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በመንጌ ወረዳ ሁለት ቀበሌዎች ላይ የተገነባው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትም 12 የውሃ ቦኖዎችን ያካተተ ሲሆን ከ11 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት አንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ በ10 ወራት ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀ መሆኑን ገልፀው ፕሮጀክቱ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበትም አስታውቀዋል።

ፋሮ ፋውንዴሽን በወረዳው የተለያዩ የልማት ስራዎችን በማከናወን የህብረተሰቡን የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች በመመለስ አጋርነቱን እያሳዬ ነው ያሉት ደግሞ የመንጌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አጠይብ ናቸው።


 

ዛሬ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ የወረዳው ነዋሪዎች አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርጉም ዋና አስተዳዳሪው አሳስበዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም