በከተማዋ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ማደግ ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጥሮልናል -የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በከተማዋ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ማደግ ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጥሮልናል -የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች
ወላይታ ሶዶ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦የወላይታ ሶዶ ከተማ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ማደግ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
በከተማዋ በተለያየ ዘርፍ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በወላይታ ሶዶ ከተማ ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እያደገ በመምጣቱ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ አድርጓቸዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወጣት ገዛኸኝ ገብሬ እና አቶ አበራ አርካ፤ በኢንዱስትሪ ዘርፍ በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል የተሻለ ገቢ እያገኙና ኑሯቸውም እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በአነስተኛ ገቢ ይተዳደሩ እንደነበር አስታውሰው፣ በከተማው እየተነቃቃ የመጣው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለነዋሪዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ተጨማሪ አቅም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ከሚያገኙት ገቢ በመቆጠብ የራሳቸውን ሥራ የመፍጠር ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
በሪል ስቴት የግንባታ ዘርፍ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ዙፋን ሰይድ፣ ሚናሴ ዲዲምስ እና ኤልሳዬ ምልኪያስ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ቀደም ሲል የነበረው የሥራ ዕድል ጠባብ በመሆኑ ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታ ያሳልፉ ነበር።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማዋ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ተከትሎ የተጀመሩ የግንባታ ፕሮጀክቶች የአካባቢያቸውን ገጽታ የሚቀይሩ ከመሆን ባለፈ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
እነሱም ባገኙት የሥራ ዕድል ተጠቅመው ቤተሰቦቻቸውን ጭምር እያገዙ መሆናቸውን ገልጸው፣ ለአካባቢው ልማት ቀጣይነት የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ባደረገላቸው ድጋፍ በ40 ሚሊዮን ብር ካፒታል ወደሥራ እንደገቡ የተናገሩት ደግሞ የራማ ፋሚሊ ፒቪሲ፣ ኤች ዲፒ እና ፕላስቲክ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳዲቅ አብዱልሃዲ ናቸው፡፡
በአሁን ወቅት ካፒታላቸው ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ መድረሱን ጠቅሰው ከ40 ለሚበልጡ ዜጎችም ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡
የኢያሱ ያዕቆብ ኮንስትራክሽን ሥራ አስኪያጅና ባለቤት ኢንጂነር ኢያሱ ያዕቆብ በበኩላቸው፣ የከተማ አስተዳደሩ ለሪል ስቴት ግንባታ ያቀረቡትን ጥያቄ በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጽደቁ በ500 ሚሊዮን ብር ካፒታል የመጀመሪያ ዙር የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ከ370 በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።
ድርጅታቸው በከተማው የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በቅንጀት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 29 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደሥራ መግባታቸውን የገለጹት ደግሞ የወላይታ ሶዶ ከተማ ኢንቨስትመንት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቸርነት ተስፋዬ ናቸው።
ኢንቨስትመንቶቹ በአገልግሎት፣ በኢንዱስትሪ፣ በግንባታና ሌሎች ዘርፎች ላይ ያተኮሩ እንደሆነም አመልክተዋል።
በዚህም ከ1 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ያሉት ኃላፊው፣ ወጣቶችም የቴክኖሎጂ እና የክህሎች አቅማቸውን ለማሳደግ ተጨማሪ ዕድል አግኝተዋል ብለዋል።