በምግብ ራሱን የቻለ ትውልድ የመገንባት ጥረት የሀገርን ክብርና ሉአላዊነት እውን የማድረግ ቁልፍ አጀንዳ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምግብ ራሱን የቻለ ትውልድ የመገንባት ጥረት የሀገርን ክብርና ሉአላዊነት እውን የማድረግ ቁልፍ አጀንዳ ነው
ድሬዳዋ ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦ ከተረጅነት በመውጣት በምግብ ራሱን የቻለ ትውልድ የመገንባት ጥረት የሀገርን ክብርና ሉአላዊነት እውን የማድረግ ቁልፍ አጀንዳ መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት" በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው የውይይት መድረክ በድሬዳዋ ተካሄዷል።
በመድረኩ ላይ የውይይት መነሻ ሐሳብ ያቀረቡት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፤ ከተረጅነት የመውጣትን ጉዳይ መንግስት ወሳኝ ሀገራዊ አጀንዳ አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በምግብ ራሱን የቻለ ትውልድ የመገንባት ጥረት የሀገርን ክብርና ሉአላዊነት እውን የማድረግ ቁልፍ አጀንዳ መሆኑን አንስተው በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
በትውልድ ቅብብሎሽ የመጣውን በእርዳታ የመኖር የጥገኝነት አመለካከት አከርካሪ በመስበር የሀገርን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የተጀመረውን አበረታች ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር፣ ሂደቱን በሁለንተናዊና በተሟላ አስተሳሰብ መምራት ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በቂና የተሟላ የውሃ ሀብት፣ የተማረና አምራች የሆነ ወጣት የሰው ኃይል እንዲሁም ለም የመሬት ፀጋዎች ያሉባት ሀገር በመሆኗ በማልማት እድገትና ማንሰራራትን ማስቀጠል ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል።
ከተረጂነት ለመላቀቅ የሚያግዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እሴቶችን በመጠቀም፣ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በፍጥነትና በፈጠራ የተመሩ የግብርና ልማት ስራዎች በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ተጨባጭና እመርታዊ ለውጥ እያመጡ ነው ብለዋል።
በምግብ ራስን የመቻል ራዕይ ከቤተሰብ ኑሮ ለውጥ እንደሚጀምር ጠቅሰው፤ ዜጎች በሰፊው አምራች እንዲሆኑ፣ የተመረተውን በአግባቡ በመጠቀምና በመቆጠብ መጠቀም እንዲችሉ እንዲሁም ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገር እንዲችሉ መደገፍ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዋናው መሠረታዊ ጉዳይም ያሉንን አቅሞች በመለየትና ህዝብን ወደ ላቀ ምርታማነት ደረጃ በማሸጋገር በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ አስተሳሰብና አተገባበር በላቀ ደረጃ ማስቀጠል መቻል መሆኑን አስታውቀዋል።