በተሳሳተ መንገድ ጫካ በመግባት በፈፀምነው ጥፋት በመጸጸት የልማት አርበኛ ለመሆን ተዘጋጅተናል-የቀድሞ ታጣቂዎች - ኢዜአ አማርኛ
በተሳሳተ መንገድ ጫካ በመግባት በፈፀምነው ጥፋት በመጸጸት የልማት አርበኛ ለመሆን ተዘጋጅተናል-የቀድሞ ታጣቂዎች
ኮምቦልቻ፤ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦በተሳሳተ መንገድ ጫካ በመግባት በፈፀምነው ጥፋት በመጸጸት የልማት አርበኛና የሰላም አምባሳደር ለመሆን ተዘጋጅተናል ሲሉ የአማራ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች ተናገሩ።
በአማራ ክልል ጫካ ገብተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል በኮምቦልቻ የተሃድሶ ስልጠና መውሰድ ጀምረዋል።
በተሳሳተ መንገድ ጫካ በመግባት በፈፀምነው ጥፋት በመጸጸት የልማት አርበኛና የሰላም አምባሳደር በመሆን ህዝብን ለመካስ ተዘጋጅተናል ብለዋል።
ከቀድሞ ታጣቂዎቹ መካከል አሸናፊ ደሳለኝ፥ ህዝቡ የሚፈልገው ሰላምና ልማት መሆኑን በተግባር አሳይቶናል ሲል ተናግሯል።
በተሳሳተ መንገድ ጫካ በመግባት ህዝብን ለእንግልት፣ዘረፋና ችግር ዳርገናል ነው ያለው።
በዚህም የመንግስትን ጥሪ ተቀብለን ሰላምን በማስከበርና ልማትን በመደገፍ ለመካስ ተዘጋጅተናል ብሏል።
ታጣቂ አለፉ ንጉሴ እና ሃምሳ አለቃ ሞላ ጎሹ በበኩላቸው፥ ለአማራ ህዝብ እንታገላለን በሚል የተሳሳተ ፕሮፓጋንዳ በርካታ ወጣቶች መታለላቸውን አንስተዋል።
የህዝብን ንብረት ከማውደም፣ከመዝረፍና እገታ ውጭ ሌላ አላማ አለመኖሩንም ተናግረዋል።
በርካቶች በጥፋታቸው በመጸጸት የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ስለመምጣታቸውም ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አማካሪ ኮሎኔል ባምላኩ አባይ፤ በክልሉ በርካታ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭ በመቀበል ስልጠና እየወሰዱ ወደ ማህበረሰቡ እየተቀላቀሉ መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ መንግስት ለሰላም በሩ ክፍት በመሆኑ ጫካ ያሉ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የስልጠና ዳይሬክተር ብርሃኑ ተስፋዬ፤ በተለያዩ አካባቢዎች የቀድሞ ታጣቂዎችን በመቀበል የተሃድሶ ስልጠና እንዲወስዱና ህብረተሰቡን እንዲቀላቀሉ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ ህዝቡን በልማት መካስ እንዳለባቸው በማሳሰብ በቀጣይም ተመሳሳይ ስራዎች የሚቀጥሉ መሆኑን ገልጸዋል።