ቀጥታ፡

በክልሉ ፕሮጀክቶችን ባጠረ ጊዜ በማጠናቀቅ የሕዝቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ ነው 

ዓለምገበያ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የልማት ፕሮጀክቶችን ባጠረ ጊዜ በማጠናቀቅ የሕዝቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ።

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በስልጤ ዞን ሳንኩራ ወረዳ ያስገነባው የብዝኃ መንደር የንጹሕ መጠጥ ውኃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ተመርቋል። 

ፕሮጀክቱ ከ430 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ሲሆን፣ በ11 ቀበሌዎች ከ31 ሺሕ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል።


 

ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ መንግሥት የልማት ፕሮጀክቶችን ግንባታ ጀምሮ ባጠረ ጊዜ በማጠናቀቅ የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል። 

ለዚህም አዲስ የተመረቀው የሳንኩራ የብዝኃ መንደር የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ፕሮጀክቱ ለረዥም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥም የአካባቢው ማኅበረሰብ በተገቢው መንገድ የመንከባከብ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለሰው ልጆች ሕልውና መሠረት በሆነው የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

የውኃ ሀብትን በብቃት በማስተዳደርና ከብክለት በመጠበቅ ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል አሠራር ተዘርግቶ እየተተገበረ እንደሚገኝም አክለዋል።

የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ፣ ባለፉት 5 ዓመታት በመንግሥትና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ የዞኑን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ሽፋን ለማሳደግ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል። 


 

በመንግሥት ድጋፍ 25 የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ከ246 ሺሕ በላይ ሰዎች ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል። 

በዚህ በጀት ዓመት ብቻ ከማኅበረሰቡ ከ298 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ የውኃ አቅርቦት ችግርን የሚቀርፉ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።

በሳንኩራ ወረዳ የጀጀብቾ ለምለም ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ፈቱ ኮርማ፤ ከዚህ ቀደም በነበረው የንጹሕ መጠጥ ውኃ እጥረት ምክንያት ረዥም ርቀት ለመጓዝ ይገደዱና ለተለያዩ እንግልቶች ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰዋል። 

ዛሬ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ፕሮጀክት ይህንን ችግራቸውን በዘላቂነት የሚፈታላቸው በመሆኑ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

በዚሁ የምረቃ መርሐ ግብር ላይ የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳው ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም