በዞኑ የሻይ ልማትን በማስፋፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የሻይ ልማትን በማስፋፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
መቱ፤ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦በኢሉአባቦራ ዞን የሻይ ልማትን በማስፋፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
በዞኑ 974 ሄክታር አዲስ መሬት ላይ የሻይ ችግኝ የሚተከል መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
የዘንድሮው የሻይ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የዞንና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በኢሉአባቦራ ዞን መቱ ወረዳ፣ ቀዎና ጫቱ ቀበሌ በይፋ ተጀምሯል።
በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የኢሉአባቦራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ እንደገለጹት፤ በዞኑ የሻይ ልማትን በማስፋፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ዞኑ ለልማቱ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የሻይ ችግኞችን በስፋት በማዘጋጀትና ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት የመትከል ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዘንድሮ በአምስት ወረዳዎች በሚካሄደው የሻይ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 974 ሄክታር አዲስ መሬት ለማልማት ታቅዷል ብለዋል።
በዞኑ እንደ አንድ ትልቅ የግብርና ኢኒሼቲቭ ተደርጎ የተጀመረውን የሻይ ልማት በኩታ ገጠም አሰራር በማስፋፋት ምርታማነትን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ዋና አስተዳዳሪው አውስተዋል።
ባለፉት ዓመታት የተተከሉት ችግኞች አሁን ላይ ለለቀማ የደረሱ በመሆናቸው፣ አርሶ አደሩ ምርቱን በወቅቱ መሸጥ እንዲችል ከጉማሮ ሻይ ፋብሪካ ጋር የገበያ ትስስር መፈጠሩን አቶ እንዳልካቸው ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ልማቱ በተስፋፋባቸው ወረዳዎች አዲስ የሻይ ፋብሪካ የሚቋቋምበትን ሁኔታ ለማመቻቸት አስተዳደሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ነመራ ቡሊ በበኩላቸው፤ የክልሉ መንግሥት የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በአጭር ጊዜ ያረጋግጣሉ ብሎ ካተኮረባቸው የግብርና ኢኒሼቲቮች መካከል የሻይ ልማት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸዋል።
የሻይ ምርት ለውጭ ገበያ ጭምር የሚቀርብ በመሆኑ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸው፤ በተለይም በኢሉአባቦራ፣ በቡኖ በደሌና በጂማ ዞኖች ባለፉት ዓመታት የተጀመረውን የሻይ ልማት ስራ ይበልጥ ለማስፋት የክልሉ መንግሥት አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በመቱ ወረዳ የልማቱ ተሳታፊ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ዋሴ ለማና አቶ ግርማ ታምሩ በሰጡት አስተያየት፤ የሻይ ልማት የተሻለና አስተማማኝ ገቢ የሚያስገኝ በመሆኑ በልማቱ ላይ ያላቸው ተነሳሽነት በእጅጉ ማደጉን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል የተከሏቸውን የሻይ ተክሎች በሚገባ በመንከባከብ፣ ምርቱን በዘላቂነት በመሰብሰብና ለፋብሪካ በማቅረብ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ በትጋት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።