የቀድሞ ታጣቂዎች የሰላም ዘብ በመሆን የበደሉትን ህዝብ ለመካስ በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የቀድሞ ታጣቂዎች የሰላም ዘብ በመሆን የበደሉትን ህዝብ ለመካስ በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል
ጎንደር ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦የቀድሞ ታጣቂዎች ከስልጠና በኋላ ከምንም በላይ የሰላም ዘብ በመሆን የበደሉትን ህዝብ ለመካስ በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል ሲሉ የሰላም ሚኒስትሩ መሀመድ እድሪስ ገለጹ።
የሠላም ሚኒስትሩ መሀመድ እድሪስ፤ የመንግስትን የሠላም ጥሪ የተቀበሉ የአማራ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎችን በብሔራዊ ተሀድሶ ማዕከል የጠዳ ጊዜያዊ ማሰልጠኛ ማዕከል በመገኘት የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ የመረከብ፣ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የማድረግና የመልሶ ማቋቋም(ዲዲአር) ፕሮግራምን አስጀምረዋል።
ሚኒስትሩ በተሃድሶ ስልጠናው ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ መንግስት የሠላም ጥሪውን የተቀበሉ ታጣቂዎች የሠላም አምባሳደር በመሆን ህዝባቸውን እንዲክሱ የማቋቋም ስራ እያከናወነ ነው።
የቀድሞ ታጣቂዎች ሠላምን አማራጭ በማድረግ የህዝብን ጥቅም በማስቀደም ለሠላም ያደረጉት አበርክቶ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ከስልጠና በኋላ ከምንም በላይ የሰላም ዘብ በመሆን የበደሉትን ህዝብ ለመካስ በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የብሄራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን ፤ መንግስት ለሠላም ባለው ጽኑ አቋምና ፍላጎት የሠላም ጥሪውን ተቀብለው የገቡ የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሀድሶ ስልጠና እንዲያልፉ በማድረግ ሰላማዊ ህይወት እንዲመሩ እያደረገ ነው ብለዋል።
ብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽኑ በአማራ ክልል የሠላም ጥሪውን የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ በማቋቋም ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል ።
በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የአስተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር)፤ በክልሉ የሠላም ጥሪውን ተቀብለው የገቡ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ በማቋቋም የሠላም ዘብ ሆነው እንዲሰሩ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ክልሉ አሁን ላይ ወደ አስተማማኝ ሠላም በመሸጋገሩ በርካታ የልማት ተግባራትን ማከናወን የተቻለበት ሁኔታ መፈጠሩን አመልክተዋል።
የክልሉ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ በሪሁን መንግስቴ፤ የሠላምን አማራጭ በመቀበል ወደ ክልሉ የገቡ የቀድሞ ታጣቂዎች የሠላም አምባሳደር በመሆን እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል ።
የቀድሞ ታጣቂዎች የሠላም አማራጭ መከተላቸው ለክልሉ የሠላም ግንባታ ስራ አስተዋጽኦው የላቀ ነው ብለዋል።
የሠላም ጥሪውን ተቀብለው ከገቡ የቀድሞ ታጣቂዎች መካከል ባዬ ቀናው፤ በተከተልነው የተሳሳተ መንገድ ህዝብና መንግስትን በድለናል ብሏል።
የሠላም ጥሪውን የተቀበልነው ለሠላም ካለን ቁርጠኛ አቋም በመሆኑ በልማት ስራዎች በመሳተፍ ህዝብና መንግስትን ለመካስ ዝግጁ ነን ሲል አክሏል።
በተሀድሶ ስልጠና ማስጀመሪያ ስነ-ስርአቱ ላይ የፌዴራል፣ የክልልና የጎንደር ከተማ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አመራሮች ተገኝተዋል።