የኢትዮጵያና አሜሪካን ታሪካዊ ግንኙነት ወደላቀ አጋርነት ማሸጋገር ያስቻለ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ ተሰርቷል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና አሜሪካን ታሪካዊ ግንኙነት ወደላቀ አጋርነት ማሸጋገር ያስቻለ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ ተሰርቷል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያና አሜሪካን ታሪካዊ ግንኙነት ወደላቀ አጋርነት ማሸጋገር ያስቻለ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ መሰራቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያን የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ግንኙነት ወደላቀ ምዕራፍ ያሸጋገረ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ መሰራቱንም ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው፤ በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መድረክ የተከናወኑ ዐበይት ክንውኖችን በማስመልከት ለመገናኛ ብዙኅን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፤ ባለፈው ሳምንት በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መድረኮች ላይ የኢትዮጵያን ትብብር፣ አጋርነትና የኢንቨስትመንት ምቹነት ያረጋገጡ ሥራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የግንኙነት መድረኮቹም ጠንካራና ንቁ ዲፕሎማሲ ተሳትፎ ማድረግ ያስቻሉ እንደነበር አስታውሰዋል።
ለአብነትም በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል የተደረጉ የሁለትዮሽ ስምምነቶች የሀገራቱን ከ120 ዓመታት በላይ የተሻገረ ታሪካዊና ጠንካራ ወዳጅነት ዘላቂና ተቋማዊ ማድረግ ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።
የሀገራቱ የሁለትዮሽ መዋቅራዊ የምክክር መድረክና ስምምነትም ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነትን በማጠናከር ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
በሁለትዮሽ ስምምነቱም የሀገራቱን ንግድና ኢንቨስትመንት፣ የፀጥታና መከላከያ ትብብር ወደላቀ ምዕራፍ በማሸጋገር የጋራ የኢኮኖሚ ብልፅግናን ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ እንደነበር አንስተዋል።
በኢትዮጵያና አሜሪካ መንግስታት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የተደረገው የዲፕሎማሲ ምክክርም ታሪካዊ ወዳጅነትን ወደላቀ አጋርነት ለማሸጋገር ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን አብራርተዋል።
በሁለትዮሽ መድረኮቹም የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገትና ብልፅግና ሞዴል እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ ገለፃ መደረጉን አስረድተዋል።
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ ያደረጉት ይፋዊ ጉብኝትም የሀገራቱን ታሪካዊ ወዳጅነት ይበልጥ የሚያጎለብት የትብብር ስምምነቶች የተፈረመበት መሆኑን ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 80ኛ ዓመትን በማስመልከትም የኢትዮጵያን መስራችነት፣ የሰላም ማስከበር ስኬታማ ተልዕኮና የጋራ ታሪክ የሚያሳይ ልዩ የቴምብር ስብስብ ማሳተሟን ጠቅሰዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ለባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ትብብር ያላትን ቁርጠኝነትና ታሪካዊ ትስስር የዘከረ መሆኑን ተናግረዋል።
በሕንድ በተካሄደው የብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባም ኢትዮጵያ ሁሉንም ሀገራት በፍትሐዊነት የሚያገለግል ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ ያላትን አቋም ማንፀባረቋን አስረድተዋል።
ከብሪክስ ስብሰባ በተጨማሪ ከአባል ሀገራቱ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችሉ ፍሬያማ ውይይቶች መካሄዳቸውን ተናግረዋል።
በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲም በደቡብ አፍሪካና ሳዑዲ አረቢያ ያሉ ዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ የሚያስችሉ ውይይቶች መካሄዳቸውንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያን ፍትሐዊ፣ ሕጋዊ፣ መልክዓ ምድራዊና ታሪካዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለማስገንዘብ የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።