የሕክምና ሙከራዎች ፈቃድ የመስጠትና የቁጥጥር ሥርዓቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚያስችል ሥርዓት ተዘርግቷል - ኢዜአ አማርኛ
የሕክምና ሙከራዎች ፈቃድ የመስጠትና የቁጥጥር ሥርዓቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚያስችል ሥርዓት ተዘርግቷል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦አዳዲስ የሕክምና ሙከራዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ፈቃድ የመስጠትና የቁጥጥር ሥርዓቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋቱን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የሕክምና ሙከራ የቁጥጥር አሠራር የምክክር መድረክ ላይ አዲስ የተገነባውን የሕክምና ሙከራ የኦንላይን ማመልከቻ ሥርዓት (Online Application System) ማስጀምሪያ መርሃ ግብር አካሄዷል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬሕይወት አበበ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ደህንነታቸውና ፈዋሽነታቸው የተረጋገጡ አዳዲስና በሙከራ ላይ የሚገኙ የሕክምና መሣሪያዎች፣ መድኃኒቶችና ሌሎች ግብዓቶች በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው።
አዳዲስ የሕክምና ሙከራዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ፈቃድ የመስጠትና የቁጥጥር ሥርዓቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋቱን ተናግረው፤ ይህም ለሕብረተሰቡ ጤናና ደህንነት መጠበቅ ጉልህ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል።
ዛሬ ይፋ የተደረገው የኦንላይን የቁጥጥር ስርዓትም የሕክምና ሙከራዎች ፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር አገልግሎትን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለኢትዮጵያ የሚቀርቡ የሕክምና ሙከራ ፈቃድ አገልግሎት ጥያቄዎች እየጨመሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ መተግበሪያው ሀገሪቱ የምታደርጋቸውን ዓለም አቀፍ ትብብሮች ይበልጥ ያጠናክራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ በበኩላቸው፤ አዳዲስ የሕክምና ሙከራዎች የሕብረተሰቡን ጤናና ደህንነት ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
የሕክምና ሙከራዎች ፈቃድና ቁጥጥርን በዓለም አቀፍ መስፈርቶች መሠረት ዲጂታላይዝ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት ውጤቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል።
ለአብነትም የማርበርግ ቫይረስ ሕክምናን ወደ ተግባር ለማስገባት ፈጣን ምላሽና ቀልጣፋ አገልግሎት በመሰጠቱ የቫይረሱን ስርጭት መግታት መቻሉን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በሕክምና ሙከራ አገልግሎት ዘርፍ ከአፍሪካ ተመራጭ ሀገር ለመሆን በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።