ቀጥታ፡

በክልሉ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን የሚያረጋግጡ የመደመር መንግስት ሀገራዊ ኢኒሼቲቮች እየተተገበሩ ነው

ቴፒ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን የሚያረጋግጡ የመደመር መንግስት ሀገራዊ ኢኒሼቲቮች በክልሉ እየተተገበሩ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።

በክልሉ ቴፒ ከተማ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የብልጽግና ፓርቲ የቅስቀሳና የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።


 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በሰልፉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የመደመር መንግስት እኩል የምንደመጥበትን ምቹ አውድ ፈጥሯል ብለዋል።

በዚህም ክልሉ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት አግኝቶ ያደሩ መሠረተ ልማቶችን ከማጠናቀቅ ባለፈ አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶችን አቅዶ በመተግበር ሕዝብን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ክልሉ ያለውን ጸጋ በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማምጣትና ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችሉ ትላልቅ ሀገራዊ ኢኒሼቲቮችን በመተግበር ላይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በፓርቲው መሪነት የተገኙ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ትሩፋቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም በጠቅላላ ምርጫው ህዝቡ ለፓርቲው ይሁንታ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን በበኩላቸው እንዳሉት፤ ፓርቲው የሕዝቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው።


 

የህዝብን የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ በመመለስ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በብልጽግና ፓርቲ መሪነት ህብረተሰቡን በልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሕዝቡ በምርጫው ዕለት በነቂስ ወጥቶ ድምጹን ለፓርቲው በመስጠት ከጎኑ እንዲሆንም ጠይቀዋል።

በክልሉ መልካም እሴቶችንና ወንድማማችነትን እያጎለበተ ያለው ብልጽግና ፓርቲ በዞኑ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ አድርጓል  ያሉት ደግሞ የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ ናቸው።


 

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተፈጠረው ፍትሐዊ የመልማት ዕድል ዞኑ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ገልጸው፣ የአካባቢውን እምቅ የተፈጥሮ ጸጋ ወደ ኢኮኖሚ ምንጭነት ለመቀየርም በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም