ቀጥታ፡

የመጀመሪያውን የምርጫ ካርዳችንን የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለሚያረጋግጥ ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት እንጠቀምበታለን 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦ የመጀመሪያውን የምርጫ ካርዳቸውን የሀገርን ልማትና ዕድገት በማፋጠን የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለሚያረጋግጥ የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት እንደሚጠቀሙበት የአዲስ አበባ ወጣቶች ገለጹ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24/2018 ዓ.ም መራጮች ድምፅ ይሰጡበታል ተብሎ የሚጠበቀው ጠቅላላ ምርጫ ውስን ቀናት ቀርተውታል።

የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባም በተለያዩ ምዕራፎች በማካሄድና በማራዘም ከየካቲት 28 እስከ ሚያዚያ 24 ቀን 2018 ዓ.ም  ሲካሄድ ቆይቶ ተጠናቋል።

በዲጂታል "ምርጫዬ" መተግበሪያና በየምርጫ ጣቢያዎች በአካል በመገኘት ከ50 ሚሊየን 514 ሺ በላይ ዜጎች ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ መውሰድ ችለዋል።

በጠቅላላ ምርጫው 47 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች 10 ሺህ 934 ዕጩዎችን በማስመዝገብ በመገናኛ ብዙኅን አማካኝነት የፖሊሲ አማራጭ ሃሳባቸውን ለህዝብ በማስተዋወቅ ላይ ናቸው።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ታዛቢነት ዕውቅና የተሰጣቸው 55 የሀገር ውስጥ ድርጅቶችም በተለያዩ አካባቢዎች ከ60 ሺህ 277 በላይ ወኪሎችን አሰማርተዋል።

በመራጮች ትምህርት ላይ ዕውቅና የተሰጣቸው 169 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም ለመራጩ ህዝብ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና ስልጠና እየሰጡ ይገኛል።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ለኢዜአ እንዳሉት፤ ጠቅላላ ምርጫው ሕገ-መንግሥታዊ የመምረጥ መመረጥ መብት በአደባባይ የሚታይበት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ልምምድ መገለጫ ነው።

ለዚህም በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ ማዕከላት በአካልና በዲጂታል አማራጭ የምርጫ ካርድ በማውጣት ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን ዝግጅት እንዳደረጉ ገልጸዋል።

በሂደቱም የሀገርን ዘላቂ ልማትና ዕድገት በማፋጠን የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለሚያረጋግጥ የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ እንደሚሰጡ አረጋግጠዋል።

የ12ኛ ክፍል ተማሪዋ ወጣት መቅደላዊት ሁሴን፤  ምርጫ የሕገ-መንግሥታዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ልምምድ መገለጫ ነው ብላለች።

በዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ በወሰደችው የምርጫ ካርድ የተሻለ የፖሊሲ አማራጭ ላለው የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀቷን ገልፃለች።

ወጣት ዳዊት ወንደሰን በበኩሉ፤ በምርጫ ሂደት ዜጎች የሚኖራቸው የነቃ ተሳትፎ የሀገርን ዘላቂ ሰላምና ዕድገት ለመበየን የማይተካ ሚና እንዳለው ተናግሯል።

በጠቅላላ ምርጫውም ሕገ-መንግሥታዊ መብቱን በመጠቀም ድምፅ እንደሚሰጥና ለምርጫው ስኬትም ገንቢ ሚና እንደሚወጣ አረጋግጧል።

ወጣት ዳግማዊት ዳንኤልም፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ  ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እንደወጣት የሚጠበቅባትን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብላለች።

ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ምርጫዎች ድምፅ ሰጥቶ እንደማያውቅ ያስታወሰው ደግሞ ወጣት ምህረቱ በቀለ ነው።

በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫም ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፅ መስጠት የሚያስችለውን ካርድ በመውሰድ ለሀገር ዕድገትና ወጣቶች ተጠቃሚነት ይበጃል የሚለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀቱን አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም