ቀጥታ፡

የምርት ጥራት ደረጃ ማረጋገጫ መተግበሪያው የኢትዮጵያን የንግድ አፈፃጸም ውጤታማነት የሚያልቅ ነው 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦አዲሱ የምርት ጥራት ደረጃ ማረጋገጫ መተግበሪያ የኢትዮጵያን የንግድ አፈፃጸም ውጤታማነት የሚያልቅ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር መሠረት በቀለ (ዶ/ር) በተገኙበት የምርት ጥራት ደረጃን በኦንላይን ማረጋገጥ የሚያስችል መተግበሪያ ተመርቋል።


 

የንግድና  ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ የምርትና አገልግሎት ጥራትን ማረጋገጥ የመደመር መንግስት ማዕከል ነው ብለዋል።

በዚህም ባለፉት የለውጥ ዓመታት የኢትዮጵያን የንግድ ሥርዓት በማዘመን የምርት ጥራትን ከውጤታማ አፈፃጸም የሚያጣጥም ስኬት መገኘቱን ገልጸዋል።

አዲሱ የምርት ጥራት ማረጋገጫ የኦንላይን መተግበሪያም አገልግሎትና የምርት ጥራቶችን በላቀ አፈፃጸም መምራት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

እስከ አሁንም በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በርካታ አገልግሎቶች በዲጂታል ሥርዓት እየተሰጡ መሆናቸውን አንስተዋል። 

ይህም የኢትዮጵያን የንግድ ሥርዓት በማዘመን አይነተኛ ሚና እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ለውጤት የበቃው የምርት ጥራት ደረጃ ማረጋገጫ መተግበሪያም የወጪና የገቢ ንግድን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳልጥ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም