በእርሻ ኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩ ዜጎች በተፈጠረላቸው የስራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በእርሻ ኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩ ዜጎች በተፈጠረላቸው የስራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል
አብርሃጅራ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦ በተፈጠረላቸው የስራ እድል ዘላቂ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ እንደሚገኙ በምዕራብ ጎንደር ዞን በእርሻ ኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩ ዜጎች ተናገሩ ።
በዞኑ ምዕራብ አርማጭሆ በድርማጋ የእርሻ ኢንቨስትመንት ስራ አስኪያጅ የሆነው ወጣት አስቻለው ደሴ ለኢዜአ እንደገለጸው ፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት በድርጅቱ በተፈጠረለት ቋሚ የስራ እድል ተጠቃሚ ሆኗል።
"በሚከፈለኝ ወርሃዊ ደመወዝና ዓመታዊ ክፍያ ቤተሰቤን ከማስተዳደር ባለፈ በዘርፉ የራሴን ስራ ለመጀመር ዝግጅት እያደረኩ ነው" ሲል ገልጿል።
በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች በመዘዋወር በእርሻ ልማት የስራ ዕድል ተጠቃሚ የሆነው ወጣት ካሳሁን ደሳለኝ በበኩሉ፣ በዘር፣ በአረምና በሰብል ስብሰባ ወቅት በአካባቢው በሚፈጠረው የስራ እድል እንደሚሰማራ ነው የሚናገረው።
በተለይም በሰሊጥ፣ በጥጥ፣ አኩሪ አተርና ሌሎች ሰብሎች በሚሰብሰቡበት ወቅት እስከ 180 ሺህ ብር እንደሚያገኝ ነው የተናገረው።
ባገኘው ገቢም አነስተኛ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ በመክፈት የቤተሰቦቹን ኑሮ ከማሻሻል ባለፈ ተጨማሪ ሀብት በመፍጠር ሒደት ላይ መሆኑን አስረድቷል።
ከመንግስት በተሰጣቸው 481 ሄክታር መሬት ላይ ሰሊጥ፣ ጥጥ፣ አኩሪ አተርና ሌሎች ምርቶችን እያመረቱ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በዘርፉ የተሰማሩት አቶ ቴዎድሮስ አለማየሁ ናቸው።
በእርሻ ስራው በየዓመቱ ለሁለት ሺህ ዜጎች ጊዜያዊ ፤ለ29 ዜጎች ደግሞ ቋሚ የስራ እድል በመፍጠር ከራሳቸው አልፎ ወጣቶችን ተጠቃሚ እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ተወካይ አቶ ዳንዔል አለሙ በበኩላቸው፣ በዞኑ ያለው ሰፊ የእርሻ መሬትና ተስማሚ የአየር ንብረት ለእርሻ ኢንቨስትመንት ተመራጭ እንዲሆን አድርጎታል ።
በርካታ ባለሃብቶች ወደ አካባቢው በመምጣት በዘርፉ በመሳተፍ ለወጭ ንግድ የሚሆኑ ምርቶች ላይ እየሰሩ እንደሚገኙም ነው የገለጹት ።
በዞኑ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ 976 ባለሃብቶች በዘር፣ በአረምና ሰብል ስበሰባ ወቅት 370 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ጊዜያዊና ቋሚ የስራ እድል እየፈጠሩ መሆኑን ገልፀዋል።