ቀጥታ፡

በዞኑ በመጪው መኸር ከ 641 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ የሰብል ዘር ለመሸፈን የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል

ባህር ዳር፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ጎንደር ዞን በመጪው መኸር ከ641 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በተለያየ የሰብል ዘር ለመሸፈን የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ አስፋው ይልማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል በትኩረት እየተሰራ ነው።

በዚህም ከ641 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ደጋግሞ የማረስና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በዘር ከሚሸፈነው መሬትም ከ28 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመው አሁን ላይ እንደ በቆሎ ያሉ ሰብሎችን መዝራት መጀመሩን ተናግረዋል።

የማዳበሪያና የምርጥ ዘር ግብዓትን በመጠቀም፣ የሜካናይዜሽንና አዳዲስ አሰራሮችን በመተግበር ላይ በማተኮር የታቀደውን ምርታማነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በዘር ከሚሸፈነው መሬት ውስጥ 65 በመቶ የሚሆነው መሬት በኩታ ገጠም አሰራር በቢራ ገብስ፣ በሩዝ፣ በስንዴ፣ በጤፍና በበቆሎ ዘሮች እንደሚሸፈን አስረድተዋል።

ይህም በሄክታር ከ41 ነጥብ 4 ኩንታል ያልበለጠ የነበረውን ምርታማነት ወደ 44 ነጥብ 3 ኩንታል ለማሳደግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

በሰብል ልማቱም 465 ሺህ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉ ጠቁመው፤ በየደረጃው ያለው የዘርፉ አመራርና ባለሙያም አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።

በዞኑ ፋርጣ ወረዳ ሳርና ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር የማታ ቢሰጥ፤ ከአንድ ሄክታር በላይ ማሳቸውን በዘር በመሸፈን ከ42 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚሁ ወረዳ የማይናት ቀበሌ አርሶ አደር ንጋቴ ጎሸ በበኩላቸው፤ አንድ ሄክታር ማሳቸውን በቢራ ገብስ በማልማት 45 ኩንታል  ለማምረት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ምርታማነቱን ለማሳደግም ሁለት ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ቀደም ብለው ገዝተው ማስቀመጣቸውን ጠቁመው በቀጣይም ምርጥ ዘርና ተጨማሪ ማዳበሪያ ገዝተው እንደሚጠቀሙም ገልጸዋል።

በዞኑ ባለፈው የመኸር ወቅት ከ26 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ማምረት መቻሉን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም