ቀጥታ፡

የማዳበሪያ ፋብሪካ በሀገራችን መገንባቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ያፋጥናል

ድሬደዋ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦ የማዳበሪያ ፋብሪካ በሀገራችን መገንባቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በማፋጠን ከፍተኛ ሚና አለው ሲሉ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) ተናገሩ።

“ከተረጂነት ወደ ምርታማነት” በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ የፓናል ውይይት በድሬዳዋ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፥ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የኅልውና ጉዳይ ነው።

የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥም ግብዓቶቹ በሀገራችን ይገኛሉ ነው ያሉት።

ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ እንዲመረት መንግሥት በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጉዞ በማፋጠን ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ነው ያስረዱት።

አርሶ አደሮች በክላስተር እና በምርምር የተደገፉ ሰብሎችን በማምረት ትርፍ አምራች ሆነው ስኬታማ እንዲሆኑ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

አንድም መሬት ጾም ማደር የለበትም በሚል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት አምጥተዋል ብለዋል።

ክልሎችም በመተጋገዝ፣ተሞክሯቸውን በመለዋወጥ ከተረጅነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር የሚደረግ ጥረትን ማዳበር እንዳለባቸው አመላክተዋል።

እንደ ሀገር ከተረጅነት ወደ አምራችነት መሸጋገር የማይቻልበት ምንም ምክንያት የለም ሲሉም በአጽንዖት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም