የህዝብን የልማት ጥያቄ የሚመልስና ሀገርን የሚያሻግር ፖሊሲ ላለው ፓርቲ ድምጻችንን ለመስጠት ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
የህዝብን የልማት ጥያቄ የሚመልስና ሀገርን የሚያሻግር ፖሊሲ ላለው ፓርቲ ድምጻችንን ለመስጠት ተዘጋጅተናል
ሀዋሳ ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦የህዝብን የልማት ጥያቄ የሚመልስ እና ሀገርን የሚያሻግር ፖሊሲ ላለው የፖለቲካ ፓርቲ ድምጻቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የሲዳማ ክልል ነዋሪዎች ገለጹ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ ለመስጠት ቀነ ቀጠሮ ተይዟል፡፡
ቦርዱ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረትም ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከ50 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የምርጫ ካርድ የወሰዱ ሲሆን፣ ዜጎቹም በካርዳቸው ይሆነኛል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የድምጽ መስጫውን ቀን እየተጠባበቁ ናቸው።
ኢዜአ ያነጋገራቸው በሲዳማ ክልል የቡራ እና በንሳ ወረዳ ነዋሪዎች እንዳሉት፤ በወሰዱት ካርድ ሀገር የሚያሻግር የፖሊሲ አማራጭ ያለውን ፓርቲ ለመምረጥ የድምጽ መስጫውን ቀን እየተጠባበቁ ነው፡፡
አስተያየታቸውን ከሰጡት የቡራ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል አቶ አለማየሁ አርጋታ እና አቶ አዱኛ አማቼጅ እንደገለጹት፤ በጠቅላላ ምርጫው ድምጽ በመስጠት ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም የምርጫ ካርድ በወቅቱ ወስደዋል፡፡
በድምጽ መስጫው እለትም የተሻለ የፖለሲ አማራጭ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የፓርቲዎችን የቅስቀሳና የክርክር ሂደት እየተከታተሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የበንሳ ዳዬ ከተማ ነዋሪ ወጣት ዘላለም ዘነበ፣ የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለሚያረጋግጥ ፓርቲ ድምጿን ለመስጠት ተዘጋጅታለች።
ወጣቶች ለሀገር ሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታ ያላቸውን ሚና በተግባር መወጣት እንዳለባቸው ገልጻ፣ በምርጫ ቀን ዴሞክራሲያዊ መብቷን ከመጠቀም ባለፈ ሰላማዊና ፍትሀዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩሏን ለመወጣት መዘጋጀቷን ተናግራለች።
ለወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ይበልጥ ተግቶ የሚሰራ ፓርቲን ለመምረጥም ፓርቲዎች በተለያዩ መንገዶች የሚያደርጉትን ቅስቀሳ በትኩረት እየተከታተለች መሆኑን ጠቁማለች።
ምርጫው ከሂደቱ ጀምሮ ሰላማዊ፣ ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ለመወጣት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የበንሳ ወረዳ ነዋሪ አቶ ታደሰ ጎኖሶ ናቸው።
ለሀገር ቀጣይነት ያለው እድገትና ለዜጎች ተጠቃሚነት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወሳኝ መሆኑን ያነሱት አቶ ታደሰ በዚህ ረገድም ተከታታይ ትምህርትና ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡