በኦሮሚያ ክልል በበልግ እርሻ የታቀደውን ምርት ለማግኘት የሰብል እንክብካቤና ጥበቃ ላይ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል በበልግ እርሻ የታቀደውን ምርት ለማግኘት የሰብል እንክብካቤና ጥበቃ ላይ ትኩረት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል በበልግ እርሻ የተዘሩ ሰብሎችን እንክብካቤና ጥበቃ በማድረግ የታቀደውን ምርት ለማግኘት ትኩረት መደረጉን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ባሪሶ ፈይሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በበልግ አዝመራ ከለማው 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ከ46 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዷል።
ዘንድሮ የተከናወነው የበልግ እርሻ ስራ ከዕቅድ በላይ መፈጸሙን የገለጹት ኃላፊው፣ ለዚህ ስኬት ዋነኛው ምክንያት ያለውን አቅም አሟጦ መጠቀም በመቻሉ እንደሆነ አብራርተዋል።
ለአርሶ አደሮቹ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ግብዓትና የግብርና ቴክኖሎጂዎች መቅረባቸውን አስታውሰው በተለይ የዘንድሮው የበልግ አዝመራ የዝናብ ስርጭቱ የተሻለ በመሆኑ ሰብሉ በጥሩ ቁመና ላይ እንዳለ አመላክተዋል።
በክልሉ በአሁኑ ወቅት በበልግ አዝመራው የታቀደውን ምርት ለማግኘት የሰብል ጥበቃና የእንክብካቤ ስራ ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ የፀረ-አረምና የተባይ ኬሚካሎች ለአርሶ አደሮቹ በስፋት እየቀረቡ መሆኑን አስታውቀዋል።
እንዲሁም አርሶ አደሮቹ ሰብሉን በቤተሰብ ደረጃና ከአካባቢያቸው ነዋሪዎች ጋር ሆነው በጋራ እየተንከባከቡ መሆኑን ገልጸዋል።
በበልጉ የለማው ሰብል ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ እንደ ግሪሳ ወፍ እና መሰል ተባዮችን አስቀድሞ ለመከላከል፣ በዘርፉ ባለሙያዎች አማካኝነት አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ኃላፊው አክለው ገልጸዋል።
ለዘንድሮው የበልግ እርሻ ስኬታማነት በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችና አመራሮች የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ የእርሻ መሬትን አስቀድሞ ከማዘጋጀት ጀምሮ ለአርሶ አደሩ ቀጣይነት ያለው ሙያዊ ድጋፍና ክትትል መደረጉንም ነው የጠቀሱት።
በክልሉ የበልግ እርሻ በስፋት ከሚከናወንባቸው 11 ዞኖች መካከል ምስራቅ ቦረና፣ ጉጂ፣ አርሲ፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ፣ ምስራቅ ባሌ እና ምስራቅ ሸዋ ዞኖች ይጠቀሳሉ።