ሀገር የተሟላ ክብርና ሉአላዊነት ሊኖራት የሚችለው ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት መውጣት ሲቻል ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር የተሟላ ክብርና ሉአላዊነት ሊኖራት የሚችለው ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት መውጣት ሲቻል ነው
ድሬዳዋ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገር የተሟላ ክብርና ሉአላዊነት ሊኖራት የሚችለው ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት መውጣት ሲቻል ነው ሲሉ በድሬዳዋ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማእረግ የመንግስት ተጠሪ ኢብራሂም የሱፍ ገለጹ።
"ከተረጅነት ወደ ምርታማነት" በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና ግብርና ሚኒስቴር የተዘጋጀው የውይይት መድረክ በድሬዳዋ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በድሬዳዋ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማእረግ የመንግስት ተጠሪ ኢብራሂም የሱፍ፤ በለውጡ ዓመታት በመደመር እሳቤ የህዝብን ተጠቃሚነት እውን ያደረጉና ሀገርን ወደ ማንሰራራት የወሰዱ ስኬቶች ተመዘግበዋል ብለዋል።
በተለይም በስንዴ ልማት የላቀ ስኬት ስለመመዝግቡ አንስተው በተለያዩ የግብርና ኢንሸቲቮች ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የመሸጋገር ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።
ለውጡ እየተመራበት ያለው የመደመር እሳቤ የዜጎችን ተጠቃሚነት እንዲሁም የሀገርን እድገትና ማንሰራራት ለማሳለጥ ያስቻለ ስኬታማ አቅጣጫ መሆኑን ያሳየ መሆኑንም ተናግረዋል።
በምግብ ራስን የመቻል ጥረት የሀገር ክብርና የትውልድ ዋስትና መሰረት መሆኑን በፅኑ በማመን መንግስት ለስኬቱ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተረጅነት የመውጣት ጉዳይ የዜጎችን ክብርና የሀገርን የወደፊት እጣ ፋንታ የሚወስን ወሳኝ ሀገራዊ አጀንዳ በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በመሆኑም ሀገር የተሟላ ክብርና ሉአላዊነት ሊኖራት የሚችለው ከተረጅነት መውጣት ሲቻል መሆኑን አንስተው የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር የሚካሄዱ መሰል መድረኮች ለሀገር የሚጠቅሙ ጥልቅ ሃሳቦች የሚነሱበት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም እንደ ሀገር ከተረጂነት ለመውጣት የሚደረጉ ጥረቶችንና የዜጎችን ብሩህ ተስፋ የሚያሳዩ የይዘት ስራዎችን በሚዲያ በስፋት ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከተረጂነት በመውጣት ምርታማነትን በማሳደግ እድገትና ማንሰራራቷ ቀጣይነት እንዲኖረው በስፋትና በጥልቀት የይዘት ስራዎችን ተደራሽ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በመድረኩ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፣ የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ሮዛ ዑመር፣ የፌዴራልና የክልል የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ከድሬዳዋ አሥተዳደር፣ ከሶማሌ፣ ሐረሪ እና አፋር ክልሎች የተውጣጡ በርካታ አርሶ አደሮች ተገኝተዋል።