ከተረጂነት መላቀቅን የክብር ጉዳይ አድርጎ መትጋት ይገባል - ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ከተረጂነት መላቀቅን የክብር ጉዳይ አድርጎ መትጋት ይገባል - ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦ ከተረጂነት መላቀቅ የሀገራዊ ሉዓላዊነትና የክብር ጉዳይ በመሆኑ ለዚሁ ስኬት በቅንጅት መትጋት እንደሚገባ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።
“ከተረጂነት ወደ ምርታማነት” በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ የፓናል ውይይት በድሬዳዋ ከተማ እየተካሄደ ነው።
ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በዚሁ መድረክ ላይ ባቀረቡት የፓናል ውይይት መነሻ ጽሑፍ፤ በዕርዳታ እህል ትውልድን ማስቀጠል እንደማይቻል ገልፀዋል።
የተሟላ ሉዓላዊነት ማለት፤ የብሔራዊ ደኅንነት ሉዓላዊነት፣ የምግብ ሉዓላዊነት፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት፣ የፖሊሲ ሉዓላዊነት፣ የባህልና የማንነት ሉዓላዊነት መሆኑንም አብራርተዋል።
በዚህ መነሻም እንደሀገር ተረጂ ሆኖ፤ ልማትን፣ ፍላጎትን፣ ነጻነትን እንዲሁም ትውልድን ማስቀጠል የማይታሰብ ነው ብለዋል።
ዕርዳታ ሰጪዎች ፍላጎታቸውንም እንድንፈፅም ማስገደዳቸው እንደማይቀር ታውቆ፤ ከተረጂነት በመውጣት አምራች መሆን የተሟላ ሉዓላዊነት ጉዳይ ነው ብለዋል።
ተረጂነት ባርነትን ስለሚወልድ ማስቀረት ይገባናልም ነው ያሉት።
ሊያጋጥሙ ለሚችሉ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች የራሳችንን ዐቅም መገንባት አለብን ሲሉም በአፅንኦት ገልፀዋል።
የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ከውስጥ ወደ ውጭ እያረጋገጡ መጓዝ ያስፈልጋልም ነው ያሉት።