ቀጥታ፡

የተሟላ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት በይበልጥ ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ድሬዳዋ፤ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦የተሟላ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈብዙ ተግባራት በይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በድሬዳዋ አሥተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ኢብራሂም ዩሱፍ አስገነዘቡ።

“ከተረጂነት ወደ ምርታማነት” በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ የፓናል ውይይት በድሬዳዋ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ባለፉት የለውጥ አመታት ተጨባጭ ውጤት ያመጡ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።

በመደመር ዕሳቤ ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ ሥራ መከናወኑም አስታውቀዋል።

በዚህም ሕዝቡን ያነቃቁ እና ተጠቃሚ ያደረጉ ስኬቶች መመዝገባቸውን ነው ያስረዱት።

የተረጂነት አስተሳሰብን በማስወገድ ረገድ የሕዝቡ ሚና የላቀ መሆኑ ታምኖበት በተከናወኑ ተግባራት በድሬዳዋ አሥተዳደር ተረጂነትን በማስወገድ አምራችነትን የሚያሰፉ ሥራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

በዚህም የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የኑሮ ውድነትን ያረጋጉ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቁመዋል።

የተሟላ ሉዓላዊነት የሚገነባው የምግብ ዋስትናም ሲረጋገጥ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከምግብ ሉዓላዊነት መረጋገጥ ጋር በተያያዘ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀው፤ለዚህም የመድረኩ ሚና የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም