ቀጥታ፡

የምርጫ ሂደቱ ምቹ የፖለቲካ ምህዳርና አስቻይ ሁኔታዎች የተፈጠሩበት ነው- የፖለቲካ ፓርቲዎች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ምቹ የፖለቲካ ምህዳርና አስቻይ ሁኔታዎች የተፈጠሩበት መሆኑን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ። 

የዘንድሮው የምርጫ ሂደትና አጠቃላይ ቅንጅት ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ያስቻለ ስለመሆኑም የፓርቲ አመራሮቹ ተናግረዋል።

አጠቃላይ የእስካሁኑን የምርጫ ሂደት አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፤ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ምቹ የፖለቲካ ምህዳርና አስቻይ ሁኔታዎች የተፈጠሩበት መሆኑን ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጸሃፊ እና የኢዜማ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ታሪኩ ድንበሩ፤ በጋራ ምክር ቤቱም ሆነ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ለምርጫው ዴሞክራሲያዊነት እና ሰላማዊነት በትብብር እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

በተለይም የጋራ ምክር ቤቱ የምርጫ እቅድ አዘጋጅቶና ኮሚቴ አዋቅሮ ወደ ስራ መግባቱን የገለጹት አቶ ታሪኩ፤ በ21 የክልሉ ዞኖች እና በ213 ወረዳዎች ምክር ቤት ተቋቁሞ የተሻለ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በምክር ቤቱ ስር የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተሻለ መልኩ ዝግጅት እያደረጉ ሲሆን፣ በሂደቱ ያጋጠሙ ችግሮችም በፍጥነት እየተፈቱ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በቀደሙት ምርጫዎች ወቅት እንደ ስጋት የሚታዩ ችግሮች የተቀረፉበት እና ምርጫው ሰላማዊ፣ ተአማኒ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት በጋራ እየሰሩ ያሉበት መሆኑን ገልጸዋል። 

የህዳሴ ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ሱራፌል እሸቱ በበኩላቸው፤ ፓርቲያቸው በ2013ቱ ምርጫ ወቅት የነበሩበትን ደካማ እና ጠንካራ ጎኖች ለይቶ የዘንድሮውን ምርጫ በከፍተኛ ዝግጅት ሲጠብቅ መቆየቱን ተናግረዋል።

ፓርቲያቸው ምርጫው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን የጠቀሱት ኢንጂነር ሱራፌል፤ ከዚህ ጎን ለጎንም የምርጫ ማኒፌስቶውን እና ፕሮግራሞቹን በተሻለ መልኩ ማስተዋወቅ መቻሉን ገልጸዋል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከአየር ሰዓት አጠቃቀም ጀምሮ የመንገድ ላይ እና የአደባባይ ቅስቀሳዎችን በተሻለ ሁኔታ ማካሄድ የሚቻልበት አስቻይ ሁኔታ የተፈጠረበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል እና የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ሰብሳቢ አቶ ኡመር አብዱራህማን፤ አጠቃላይ የዘንድሮው ምርጫ ሂደት የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ የተፈጠረበት እና የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

"የምርጫ ምህዳር አሳታፊነቱ በተለይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ነጻ የአየር ሰዓት አውጥቶ ሀሳባችንን በነጻነት ለህዝብ ተደራሽ እንድናደርግ ያመቻቸበት መንገድ እጅግ የሚበረታታ ነው" ብለዋል።

የወለኔ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ፋይሰል አብዱልዓዚዝ እንዲሁ ዘንድሮ ከምርጫ ቦርድ ጀምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉበት ዓመት መሆኑን ጠቁመዋል።

"ዘንድሮ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊ እና ግልጽ የሆነ ውድድር እንዲኖር ከማድረግ ረገድ እጅግ ጥሩ ሁኔታዎች የተፈጠሩበት የምርጫ ሂደት እየተመለከትን ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም