ቀጥታ፡

በምዕራብ ወለጋ ዞን ከ279 ኪሎ ሜትር በላይ የገጠር መንገዶች ተጠግነዋል

ጊምቢ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦በምዕራብ ወለጋ ዞን ባለፉት አሥር ወራት ከ279 ኪሎ ሜትር በላይ የገጠር መንገዶች ተጠግነው ለአገልግሎት መብቃታቸውን የዞኑ መንገዶች ጥገና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አናቶሊ ቱፋ ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ ባለፉት ዓመታት በዞኑ የገጠር መንገድ ተደራሽ ለማድረግ ሰፋፊ ሥራዎች ተከናውነዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም ከመንገድ ተደራሽነቱ በተጨማሪ በተለያዩ ምክንያቶች የተጎዱ 329 ኪሎ ሜትር መንገዶችን ለመጠገን ታቅዶ ባለፉት አሥር ወራት ብቻ 279 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመጠገን ተችሏል ብለዋል።

የመንገድ ጥገና ሥራው በ12 የመንገድ መስመሮች ላይ የተከናወነ ሲሆን እነዚህም ወረዳን ከወረዳ እንዲሁም ወረዳን ከዞኑ ዋና ከተማ የሚያገናኙ መሆናቸውን አንስተዋል።

ለጥገና ሥራው ከ56 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን የገለጹት አቶ አናቶሊ፤ ጥገና ከተደረገላቸው የመንገድ መስመሮች መካከል ከጊምቢ-ጋምቤላ-ሖማ፣ ከአይራ-ቦንደዎ እና ከወራጂሩ-አባ ኤባ የሚወስዱ መንገዶች ይጠቀሳሉ ብለዋል።

የመንገዶቹ መጠገን የአካባቢውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ከመፍታት ባለፈ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴን ማፋጠኑንና  ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

በተለይም በዞኑ ቡና በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚመረት አስታውሰው፣ የመንገዱ መገንባት አርሶ አደሩ ቡናን ጨምሮ የሚያመርታቸውን የግብርና ምርቶች በቀላሉ ወደገበያ በማጓጓዝ ተጠቃሚነቱን ያሳድጋል ብለዋል።

በዞኑ በአሁኑ ወቅት የሰፈነው ሰላም የመንገድ ጥገና ሥራውና መሰል የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጉን ያነሱት ኃላፊው፤ የተበላሹ መንገዶች ተጠግነው ለትራንስፖርት ምቹ መደረጋቸው ለሌሎች የልማት ስራዎች መፋጠንም ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

የሖማ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አሸናፊ ጀማል እንደተናገሩት፤ ለመንገዶቹ የተደረገው ጥገና ከዚህ ቀደም በብልሽት ምክንያት ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት አስቀርቷል።

የህብረተሰቡን ማህበራዊ መስተጋብርና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማሳለጥ ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል።

በአካባቢያቸው በስፋት የሚመረተውን ቡና እና ሌሎች የግብርና ምርቶችን ወደተለያዩ አካባቢዎች ገበያ አቅርበው በተሻለ ዋጋ ለመሸጥና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እንዳስቻላቸውም ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ የተጠገኑት መንገዶች ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ አስፈላጊውን ጥበቃና እንክብካቤ እንደሚያደርጉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም