ቀጥታ፡

የአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ የአካባቢውን ኢንቨስትመንት ያሳድጋል

ደብረ ማርቆስ ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦ የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ መጠናቀቅ የአካባቢውን የኢንቨስትመንት፣ የንግድና ቱሪዝም ልማት በማፋጠን  የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ነው ሲሉ የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች ገለጹ።

የከተማ አስዳደሩ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ አቶ ተመስገን ተድላ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአውሮፕላን ማረፊያው የአካባቢውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማፋጠን የላቀ ድርሻ አለው።


 

በተለይ ባለሃብቶች  ያጋጥማቸው የነበረውን የትራንስፖርት ችግር በመቅረፍ ፕሮጀክቶቻቸውን በቅርበት ለመከታተልና ፣  ምርታማነታቸውን  ለማሳደግ የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል።

በአካባቢው የሚመረቱ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በፍጥነት ወደ ገበያ ከማቅረብ በተጨማሪም የአውሮፕላን ማረፊያው አዳዲስ ባለሃብቶችን ለመሳብም መልካም እድል ይዞ መምጣቱን አስረድተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ አእምሮ በበኩላቸው፤ የአውሮፕላን ማረፊያው  የቱሪዝም ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያነቃቃ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዋናነትም የአባይ በረሃን አቋርጦ በመምጣት በአካባቢው የሚገኙ ቅርሶችን ለመጎብኘት ያጋጥም የነበረውን ችግር በመቅረፍ የጎብኝዎችን ቁጥር ለመጨመር የሚያስችል ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም የጮቄ ተራራን፣ ጥንታዊ ገዳማትና ሌሎች ቅርሶችን ለጎብኝዎች ክፍት ለማድረግም አሰጎብኝዎችን ከማደራጀት ጀምሮ ምቹ መስተንግዶ ለማቅረብ በተለየ ሁኔታ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጅነር ሙሉጌታ ይስማው በበኩላቸው፤ የአውሮፕላን ማረፊያው መገንባት የዘመናት የህዝብ ጥያቄን በመፍታት የንግድ እንቅስቃሴን ለማሳደግ የሚያስችል ነው ብለዋል።


 

አካባቢው በግብርናው ዘርፍ ትርፍ አምራች ከመሆኑም በላይ ያለውን የማዕድን ሃብት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም ከተማዋን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማእከል ለማድረግ መልካም እድል ይዞ መምጣቱን ጠቁመው ይህም በአገልግሎት ዘርፉ የተሰማሩ ግለሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል ።

በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በግንባታ ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎችን ፈጥኖ በማጠናቀቅ አካባቢውን የንግድ ማእከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም