ቀጥታ፡

በብሄረሰብ አስተዳደሩ የተገነቡ መሰረተ ልማቶች ህዝቡን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው

ሰቆጣ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ) ፦ በመንግስት የተገነቡ  መሰረተ ልማቶች የህዝቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዳስቻሉ የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የመንገድ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ መምሪያ አስታወቀ።

በብሄረሰብ አስተዳደሩ በ33 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ የተገነቡ የኮንክሪትና የተንጠልጣይ ድልድዮች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል ።

በብሄረሰብ አስተዳደሩ በምክትል አስተዳዳሪ ማዕረግ የመንገድ ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ መምሪያ ኃላፊ አቶ ፀጋው እሸቴ እንደገለፁት ፤ መንግስት የአካባቢውን ማህበረሰብ በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር ስኬታማ ስራዎችን እያከናወነ ነው።

በአሁኑ ወቅትም በ33 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነቡት በጋዝጊብላ ወረዳ የጎልሆ ወንዝ የኮንክሪት እንዲሁም የዝቋላ ወረዳ የጨዋ ተንጠልጣይ ድልድዮች መጠናቀቃቸውን አስረድተዋል።

የእነዚህ መሰረተ ልማቶች መጠናቀቅ የማሕበረሰቡን ትስስር የሚያጎለብቱ መሆኑን የገለጹ ሲሆን በክረምት ወቅት በሰው፣ በእንስሳትና ሌሎች ንብረቶች ላይ ይደርስ የነበረውን የጎርፍ አደጋ የሚያስቀር መሆኑን ገልጸዋል።

የጎልሆ ወንዝ የኮንክሪት ድልድይ ለስምንት ቀበሌዎች፤ የዝቋላ ወረዳ የጨዋ የተንጠልጣይ ድልድይ ደግሞ ለአራት ቀበሌዎች ክረምት ከበጋ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ መሆኑን አንስተዋል።

በተጨማሪም በፌደራል መንግስት ወጭ እየተገነባ የሚገኘው የሰቆጣ -ላሊበላ-ጋሸና የአስፋልት መንገድ ግንባታ መንግስት ለመንገድ መሰረተ ልማት ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት የሚያመላክት ነው ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የጤና፣ የትምህርት፣ የኤሌክትሪክ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችን በመገንባት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንደሆኑም አስረድተዋል።

በአስተዳደሩ የጋዝጊብላ ወረዳ የመስቀሎ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሞላ ማሞ እንዳሉት፤ የጎልሆ ወንዝ ድልድይ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱ ለአካባቢው ማሕበረሰብ እፎይታን የሰጠ ነው።

የድልድዩ መገንባት የክረምት ወቅት የሚከሰተውን የውሃ ሙላት በማስቀረት በተለይ የግብርና ምርቶችን ለማጓጓዝና ለገበያ ለማቅረብ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወደ አካባቢው ለማስገባት እንደሚያስችልም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም