የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በሊጉ ግርጌ ከሚገኘው አርባምንጭ ከተማ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በሊጉ ግርጌ ከሚገኘው አርባምንጭ ከተማ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ33ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል።
ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ አርባምንጭ ከተማ ከሲዳማ ቡና በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
አርባምንጭ ከተማ በ29 ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃ ይዟል። ሲዳማ ቡና በ55 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ያላሸነፈው አርባምንጭ ከተማ ማሸነፍ በሊጉ የመቆየት ተስፋውን ለማለምለም የሚያስችለውን ሶስት ነጥብ እንዲያገኝ ያደርገዋል።
ባለፉት አራት የሊግ ጨዋታዎች ላይ ከድል የራቀው ሲዳማ ቡና ዛሬ ካሸነፈ ከተከታዩ መቻል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ከፍ ያደርጋል።
ጨዋታው ለሁለቱም ቡድኖች ወሳኝ የሚባል ነው።
በሌላኛው መርሐ ግብር ነገሌ አርሲ ከምድረ ገነት ሽሬ ምሽት 12 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ነገሌ አርሲ በ51 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው ምድረ ገነት ሽሬ በ36 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
በ32ኛ ሳምንት በመቻል የ4 ለ 0 ሽንፈት ያስተናገደው ነገሌ አርሲ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እና በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት ሶስት ነጥብ ማግኘት ይኖርበታል።
በተመሳሳይ በ32ኛ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን 1 ለ 0 ያሸነፈው ምድረ ገነት ሽሬ በዛሬው ጨዋታ ድል ከቀናው ከወራጅ ቀጠና ሊወጣበት የሚችልበት እድል ሊፈጠር ይችላል።
ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
አዳማ ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
አዳማ ከተማ በ38 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል። ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ39 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በ32ኛ ሳምንት መርሐ ግብር አዳማ ከተማ በፋሲል ከነማ የ3 ለ 1 ሽንፈት ሲያስተናግድ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2 ለ 1 ረቷል።
ጨዋታው ለሁለቱም ቡድኖች ከወራጅ ቀጠና ስፍራ ፈቀቅ ለማለት ወሳኝ የሚባል ነው።
የዛሬ መርሐ ግብሮች ዋንጫ ለማንሳት እና ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ናቸው።