በዴሞክራሲ ተቋማት የተፈጠረው አስቻይ ምኅዳር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ሂደት ያላቸው ተሳትፎ እያደገ እንዲመጣ አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በዴሞክራሲ ተቋማት የተፈጠረው አስቻይ ምኅዳር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ሂደት ያላቸው ተሳትፎ እያደገ እንዲመጣ አስችሏል
አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 12/2018 (ኢዜአ) ፦በኢትዮጵያ በዴሞክራሲ ተቋማት የተፈጠረው አስቻይ ምኅዳር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ሂደት ያላቸው ተሳትፎ እያደገ እንዲመጣ ማስቻሉን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አቶ መለሰ ዓለሙ ገለጹ።
አቶ መለሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊ፣ ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊነትን የሚያረጋግጡ ዝግጅቶችን በማድረግ ወደ ትግበራ መገባቱን ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ የመገናኛ ብዙኅን በሚካሄዱ የምርጫ ክርክር መድረኮች ላይ የፖሊሲ አማራጮችን በግልፅ ለህዝብ በማቅረብ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑንም አብራርተዋል።
ከምርጫ ቦርድ፣ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ መገናኛ ብዙኅንና የፀጥታና የፍትሕ ተቋማት ጋር በምርጫው ሂደት በመርህ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት በማድረግ አስቻይ ሁኔታ በመፍጠር እየተሰራበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚዛን የጠበቀ የፉክክርና የትብብር መርህን በመከተል የሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ምክር ቤቱ እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በእስካሁኑ ሂደትም ከ50 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በመራጭነት መመዝገቡም የምርጫ ተሳትፎ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፉክክር ባለፈ ለሀገር ግንባታ መሳካት እንዲሰሩ ሀላፊነት የሚሰጥ ነው ብለዋል።
የሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ሂደት አስቻይነት የሚያረጋግጡ የማሻሻያ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በዴሞክራሲ ተቋማት የፈጠረችው አስቻይ ምኅዳርም የምርጫ ዴሞክራሲያዊነት ልምምድም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ መምጣቱን አስረድተዋል።
በሁሉም ክልሎች፣ ዞኖች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ወረዳዎች በተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤቶች አማካኝነት ሁሉም ፓርቲ እየተሳተፈ ነው ብለዋል።
በተቃራኒው አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ አይነቶች በማህበራዊ ሚዲያና መገናኛ ብዙኅን የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ሚዛናዊነት የጎደላቸው ናቸው ብለዋል።
እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከድርጊታቸው በመቆጠብ ለምርጫው ዴሞክራሲያዊነት ገንቢ ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።
መራጩ ህዝብም ድምፅ በሚሰጥበት ወቅት በንቃት በመሳተፍ ይበጀኛል ለሚለው ፓርቲ ድምፅ በመስጠት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።