መገናኛ ብዙሃን ለዴሞክራሲ ስርዓት መዳበር ሚናቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል-ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን ለዴሞክራሲ ስርዓት መዳበር ሚናቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል-ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፦መገናኛ ብዙሃን የህዝብን ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚያጎለብቱ ስራዎችን በመስራት ለዴሞክራሲ ስርዓት መዳበር ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ አስገነዘቡ።
ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስኬት የመገናኛ ብዙሃን ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣መገናኛ ብዙሃን በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውስጥ በመንገድ ጠቋሚነት፣ በችግር ፈቺነትና በአጋዥነት ትልቅ ስፍራ አላቸው።
ይህም መገናኛ ብዙሃን በማህበረሰቡ ውስጥ እጅግ የጎላ ስፍራ እና ከፍተኛ ሀገራዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው የሚያመላክት መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተለይም እንደ ምርጫ ባሉ ወሳኝ ወቅቶች ህዝቡ የመወሰን አቅሙን የሚለማመድበት፣ የስልጣን ገደቡን የሚያውቅበት እንዲሁም እሱን ተከትሎ ስርዓት የሚያሰፍንበት ምህዳር መሆኑን የማሳወቅ ትልቅ ኃላፊነት በመገናኛ ብዙሃን ላይ ይወድቃል ብለዋል።
መገናኛ ብዙሃን እውነታን የመፈተሽ፣ ህዝብን ወደ እውነታው የማምጣት፣ የደፈረሰ ሀሳብን የማጥራትና የተዛነፈ አካሄድን የመግራት ግዴታ እንዳለባቸውም ሚኒስትሯ አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የቅድመ ዝግጅት ስራ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለዓለም ህዝብ ትልቅ ትርጉምና መልዕክት ያስቀመጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም ከ50 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የምርጫ ካርዳቸውን ወስደው ድምፅ ለመስጠት በከፍተኛ ተነሳሽነት በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን በአብነት አንስተዋል።
ይህ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የመራጮች ቁጥር እና የህዝቡ ዝግጁነት ደግሞ ዴሞክራሲ የእኛ እና ለእኛ ብቻ ነው ብለው ለሚያስቡ የውጭ ሀገራት ትልቅ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው ብለዋል።
በመሆኑም በተቀሩት ጥቂት ቀናት ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ላይ የሚገኘውን ህዝብ ይበልጥ የሚያተጋ እና የሚያነቃቃ ስራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።